አብዴፓ 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን 11 የስራ አስፈጻሚ አባላትን በመምረጥ አጠናቀቀ

71
ሰመራ ህዳር 30/2011 የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) በ7ኛ መደበኛ ጉባኤው የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ 11 የስራ አስፈጻሚ አባላትን በመምረጥ ዛሬ ተጠናቀቀ፡፡ ጉባኤው ኢንጂነር አይሻ መሐመድን ሊቀመንበር አቶ አወል አርባን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) በሰመራ ከተማ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ሲያደርግ የቆየውን  7ኛ መደበኛ ጉባኤ ሲያጠናቅቅ  ከተመረጡት 11 ሰራ አስፈጻሚዎች ውስጥ የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ ሰባቱ አዲስ የስራ አስፈጻሚ አባላት ሲሆኑ ቀሪዎቹ አራቱ  ነባር አመራሮች  ናቸው፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ጉባኤው  በፓርቲው የሚታየውን የእስትራቴጂክ አመራር ድክመት፣ የተደራጀ ሌብነት እና የህግ የበላይነት ችግሮች ዙሪያ  ሰፊ ጊዜ ወስዶ መክሯል፡፡ ፓርቲው  ካለበት ችግር ለመውጣት ነባር አመራሮችን በክብር በማሰናበት በትምህርት ዝግጅታቸውና ባላቸው ብቃት ለውጡን ሊመሩ የሚችሉ  አዳዲስ ወጣት አመራሮችን በማዕካላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲካተቱ  መደረጉን ሊቀመንበሯ አስታውቀዋል፡፡ አዲሱ አመራር የዓላማ አንድነትን በመያዝ የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ የአስፋጻሚ አካለትን አደረጃጃት እንደ አዲስ በመፈተሸና  በማደራጀት የህብረተሰቡን የልማትና ዴሞክራሲ ጥያቄ ለመለስ አንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፍትህ አካላትን እንደ አዲስ በማዋቀር የህግ የበላይትን ለማረጋጋጥ እንደሚሰራ ሊቀመንበሯ አመልክተዋል፡፡ ከአጎራባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር የተፈጠሩ ግጭቶችን የባህላዊ አደረጃጀቶችንና የክልል አመራሮችን  ባሳተፈ መንገድ በመፍታት የህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) በ7ኛ መደበኛ ጉባኤ 11 የስራ አስፈጻሚ አባላትን በመምረጥ የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህም መሰረት፡-
  1. ኢንጂነር አይሻ መሃመድ
  2. አቶ አወል አርባ
  3. አቶ አሊሁሴን ወኢሳ
  4. አቶ ኢብራሂም ሁመድ
  5. አቶ አሊሁሴን ኡመር
  6. አቶ ኤለማ አቡበከር
  7. አቶ መሃመድ ሀሰን
  8. ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ
  9. አቶ ጣሃ አህመድ
  10. አቶ አህመድ መሃመድ ቦዳያ
  11. አቶ መሃመድ ጠይብ የስራ አስፈጻሚ አባላት ሆነው መመረጣቸው ታውቋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም