በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የከፋ በመሆኑ ሁሉም ሊከላከለው እንደሚገባ ተጠቆመ

75
ደብረ ማርቆስ/ጎንደር  ህዳር 29/2011 የሴቶች ጥቃት በቤተሰብ ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የከፋ በመሆኑ ሁሉም ሊከላከለው እንደሚገባ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሳሰቡ። ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ታፈረ መላኩ የሴቶችን ጾታዊ ጥቃት የማስወገድ ቀን ሲከበር እንዳሉት ሴት ልጅ ላይ የሚፈፀም ጥቃት ከተጎጂዋ ባለፈ በቤተሰብ ላይ የሚያደርሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥፋት የከፋ ነው። በመሆኑም ሁሉም ድርጊቱን ሊከላከለው እንደሚገባ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አመላክተዋል ። "ሴቶችን የበታች አድርጎ ከማየት ጀምሮ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ግርዛትና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከቤት ውስጥ ጀምሮ የሚፈጸሙ በመሆናቸው ልንከላከላቸው ይገባል" ብለዋል ። የዩኒቨርሲቲው የስርአተ ጾታ ዳይሬክተር ወይዘሪት ሰላማዊት መክብብ በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች እየተባባሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ ጠንካራ አለመሆን ለድርጊቱ መስፋፋት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ። አንዲት ሴት በምታውቀውም ሆነ በማታውቀው ግለሰብ ጥቃት ሲፈጸምባት ለሚመለከተው አካል ማሳወቅና ያገበኛል ብሎ ጥብቅና በመቆም የሁሉም ኃላፊነት እንዲሆንም ዳሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ሰባዊ መብት ኮሚሽን የባህር ዳር ቅንጫፍ ባለሙያ አቶ የኔወርቅ መንግስት " በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ሰባዊ መብታቸውን እየገፈፈ ያለ ድርጊት ነው" ብለዋል። በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የሰባዊ መብት ጥቃት ለመከላከል በኮሚሽኑ እየተደረገ ያለውን ጥረት ባለድርሻ አካላት እንዲያግዙም ጠይቀዋል ። በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ "የሴቶች የሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች በተወጣጡ ሴቶች የሰላም የንቅናቄ ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ "በአካባቢው እየታየ ያለውን የሠላም መደፍረስ ለማስቆም ሴቶች የጎላ ሚና ሊወጡ ይገባል" ብለዋል ። የከተማው ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መመሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ወርቄ ሙላቴ በበኩላቸው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል ። ሰላምን በማስፈን በኩል የሴቶች ሚና የላቀ መሆኑንም አመልክተዋል። "በአንድ አካባቢ በሚፈጠር የሰላም መደፍረስ ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶችና ህፃናት ናቸው" ያሉት ወይዘሮ ወርቄ የችግሩ ሰለባ ከመሆን በፊት ሰላምን መስበክ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም