ህገ- መንግስቱ ሊከበር ይገባል....የመቀሌ ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች

62
መቀሌ ህዳር 29/2011 ህገ መንግስቱ የህዝቦች እኩልነትና አንድነት የተረጋገጠበት በመሆኑ ሊከበር ይገባል ሲሉ  የመቀሌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጠየቁ። " በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል 13ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በክልል ደረጃ ዛሬ በመቀሌ ከተማ በህዝባዊ ሰልፍ ተከብሯል ። ከሰልፈኞቹ መካከል ወጣት ተስፋይ በሪሁን በሰጠው አስተያየት እንዳለው በህገ መንግስቱ የህዝቦች እኩልነትና አንድነት ተረጋግጧል። የህገ- መንግስቱ ነፀብራቅ የሆነው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልም የህዝቦች እኩልነት መረጋገጡን በተጨባጭ የሚያሳይ መሆኑን አመልክቷል። "ዘንድሮ በዓሉን የምናከብረው የሀገሪቱን ልማትና ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል ቃላችንን በማደስ ነው” ሲልም ጨምሮ ገልጿል። ወጣት ተስፋይ እንዳለው በአንድ ላይ መስራትና በእኩልነት ማደግ የሚቻለው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በጋራ መታገል ያስፈልጋል። ወይዘሮ መብራት ተስፋይ በበኩላቸው በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እየተከበረ ባለው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። " እለቱ በሴቶች ላይ ሲደርስ የነበረው ጭቆናና ግፍ ቀርቶ እኩልነታቸው ስለመረጋገጡ አንድ ማሳያ ነው" ያሉት ወይዘሮ መብራት የጭቆና ዘመን ተመልሶ እንዳይመጣ ወጣቶችና ሴቶች ተደራጅተው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጠቁመዋል። " በዓሉ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ውጤቶችን የምናጣጥመበትና የራሳችንን አዲስ ታሪክ የምንሰራበት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል” ያለው ደግሞ ወጣት ግርማይ ገብረስላሴ የተባለ የከተማዋ ነዋሪ ነው። ወጣት አረጋዊት በላይ በበኩሏ እየተከበረ ያለው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የተረጋገጠው ህገ- መንግስት መገለጫ መሆኑን ገልጻለች። “ህገ-መንግስቱም ሆነ በዓሉ በህዝቦች የጋራ ጥረት ሊጠበቅና ሊከበር ይገባል” ብላለች ። በበዓሉ ላይ ሰልፈኞቹ ካስተላለፏቸው መልዕክቶች መካከል "የብሔር፣ ብሔረሶበችና ህዝቦች እኩልነትና አንድነት ያብባል እንጂ በጸረ- ሰላም ኃይሎች አይቀለበስም! ፤ “የፌደሬሽን ምክርቤት ስልጣንና ተግባር ሊከበር ይገባል!” የሚሉት ይገኙበታል። ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያን ሰንድቅ ዓላማና የህወሓትን አርማ በማውለብለብ ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም