ኢትዮጵያዊ አንድነትን ወደታላቅ ከፍታ ለማሸጋገር የአገር ሰላምን መጠበቅ ይገባል- የብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች

1590

አዲስ አበባ  ህዳር 29/2011 በኢትዮጵያ የሚታየውን አግባብ ያልሆነ ልዩነት በማስወገድ ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች ተናገሩ።

13ኛው የብሔር ብሄረሰቦች በዓል ”በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ብሄራዊ ስታዲየም ዛሬ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

የበዓሉ ተሳታፊ የነበሩ እና  ከመላው አገሪቱ የተጋበዙ የብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥና ለማጠናከር የአገር ሰላምንና አንድነትን መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ እንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ቀድሞ የነበረውን የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት ባህልና እሴት የሚሸረሽር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አክለውም ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃችና ተግባራትን ለማገዝ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የበአሉ ተሳታፊ የነበሩት ሻምበል እሸቱ አያና እንዳሉት  “በጣም ደስ ይላል በብሄር ብሄረሰብ  እንደዚህ ተሰባስቦ አንድ ሆኖ ተደምሮ ተደስቶ ሲገባ በጣም ደስ ይላል።  ”

“ዛሬ ቀን ህዳር 29 እኔ እንግዲህ የራሴነ ባህል እንደዚህ እያንፀባረኩ ነው፤ትልቅ ቀን ነው የተለያዩ ባህሎችን የለበሱ ኢትዮጵያዊያን የልዩነትን አንድነት በተግባር ያየሁበት ነው” ያሉት ደሞ ሳዲቅ ሀሰን ከወለኔ ብሄረሰብ የመጡት ናቸው፡፡

ከደቡብ ክልል የጋሞ ብሄረሰብን ወክለው የመጡት አቶ መላኮ ጦጮ እና ወይዘሮ አስካለ አባተ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የተጀመረውን ልማትና ለውጥ ለማስቀጠል በአንድነት ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባዋ የበዓሉ ተሳታፊና የባህል ልብስ ዲዛይነሯ ለይላ ፋሪስ  በበኩሏ ኢትዮጵያዊያን በልዩነት ውስጥ ያለው አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል ብላለች።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።