ሰልጣኝ የፖሊስ አባላት የአቅመ ደካሞችን ሰብል ሰበሰቡ

64
ደብረ ብርሃን ህዳር 29/2011 የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ማሰልጠኛ ተቋም ሰልጣኞች በዘመቻ ሰበሰቡ። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ማሰልጠኛ ተቋም ዋ ሱፐር ኢንተንደንት ሙላቱ ጫንያለው እንደገሉጹት ሰብሉን የመሰብሰብ ሥራ የተሰራው የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ ለማድረግ ነው። በእዚህም 434 የማረሚያ ቤት ፖሊስ ሰልጣኞች በራሳቸው ተነሳሽነት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን አለልቱ ወረዳ ትናንት ተገኝተው የአቅመ ደካሞችን የስንዴና የጤፍ ሰብል ጉዳት ሳይደርስበት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል። ዋ ሱፐር ኢንተንደንት ሙላቱ እንዳሉት ባለፈው ሳምንትም 227 ሰልጣኞች ከ65 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ የደረሰ ሰብል ሰብስበዋል። በቀጣይም ከኦሮሚያ እና አማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞኖች አመራሮች ጋር በመነጋገር የደረሱ የአቅመ ደካማ ሰብሎችን ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው ያስታወቁት። በተጨማሪም የተቋሙ ሰልጣኞች ለተቸገሩና ረዳት ለሌላቸው አረጋዊያንና ተማሪዎች የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተዋል። በሰብል ስብሰባው ላይ ከተሳተፉ ሰልጣኞች መካከል ምክትል ሳጅን አብራራው መንግስቴ እንዳሉት  በራሳቸው ተነሳሽነት የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል በመሰብሰባቸው የህሊና ርካታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። "መልካም ስራን ከዚሁ መጀመራችን  በቀጣይ ከስልጠና በኋላ ለምንሰጠው ማህበራዊ አገልግሎት ጠቀሜታው ይኖረዋል" ብለዋል። በሰብል ስብሰባ ላይ ከመሳተፋቸው ባለፈ በተለያዩ ጊዜያት በሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት፣ ከተማ ጽዳትና ውበት ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። በአለልቱ ወረዳ የኮኬነስበር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰለሞን ማሞ በበኩላቸው በስምንት ሄክታር ማሳ ላይ ስንዴ፣ ጤፍና ባቄላ መዝራታቸውንና ከእዚህም ከ90 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የጤፍና ስንዴ ሰብላቸው በተመሳሳይ ወቅት ከመድረሱ ባለፈ ሰብሉን በራሳቸውም ሆነ ከፍለው ለመሰብሰብ ደጋፊና አቅም ስለሌላቸው ስጋት ውስጥ ገብተው እንደነበር ገልጸዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ማሰልጠኛ ተቋም ሰልጣኞች በትናንትናው ዕለት ከሁለት ሄክታር መሬት በላይ የስንዴ ምርታቸውን ስለሰበሰቡላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። ምርቱን ከፍለው ቢያሰበስቡ ኑሮ ከሁለት ሺህ ብር በላይ ወጭ እንደሚጠይቃቸው አርሶ አደሩ ተናግረዋል። እስካሁን በሰልጣኞቹ በተደረገላቸው ድጋፍና በራሳቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ሰብላቸውን መሰብሰባቸውን ገልጸው ሰልጣኞች ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በአለልቱ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሰይፈ አማረ በበኩላቸው በወረዳው በመኽር የተዘራው ሰብል በአብዛኛው የደረሰ ቢሆንም አቅም ደካማ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለመሰብሰብ መቸገራቸውን ጠቁመዋል። ረዳት ቤተሰብ የሌላቸውና ገንዘብ ከፍለው ለመሰብሰብ የሚቸገሩ አርሶ አደሮችን በመለየት በበፌደራል ማስልጠኛ ተቋም ሰልጣኞችና በተማሪዎች ድጋፍ ምርታቸው እንዲሰበሰብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። አቶ ሰይፈ እንዳሉት በትናንትናው እለት በሰባት ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የ14 አቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ስንዴና ጤፍ በማረሚያ ቤት ፖሊስ ሰልጣኞች ተሰብስቧል። በቀጣይም የተለያዩ በጎ አድራጊ ተቋማትንና ግለሰቦችን በማፈላለግ የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባለጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። በወረዳው ከተዘራው 28 ሺህ 587 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በአሁኑ ወቅት መሰብሰቡን የግብርና ጽህፈት ቤቱን መረጃ ያሳያል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም