በ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተገነባው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሱዳንና ጅቡቲ መሪዎች በተገኙበት ዛሬ ይመረቃል

59
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 በ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተገነባው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሱዳንና ጅቡቲ መሪዎች በተገኙበት ዛሬ ይመረቃል። ፓርኩ ከ10 ሺህ ለሚልቅ የአካባቢው ህዝብ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ጂማ  የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ዛሬ ይመርቃሉ። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል-በሽር ጂማ ተገኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው ሲደርሱም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ይፋዊ የምርቃት ስነ-ስርአቱ ከደቂቃዎች በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል። ግንባታው ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው የጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይጠናቀቅ መቅረቱ ይታወቃል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ግንባታው በመጠናቀቁ በዛሬው እለት ይመረቃል። ሲሲሲ የሚሰኘው የቻይና የግንባታ ኩባንያ በ75 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ፓርኩ በውስጡ ጨርቃጨርቅንና የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ዘጠኝ የማምረቻ ሼዶች ይኖሩታል። በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት ማምረቻዎች ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ 10 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የጅማ ከተማን ምጣኔ ኃብታዊ እንቀስቃሴ ከማሳደግ ባሻገር የአካባቢውን እድገትና የማህበረሰቡንም ገቢ ለማሻሻል የበኩሉን ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል። በተለይም በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ቡና፣  ማር፣ ቆዳ፣ ጣውላ፣ ጥጥና ሌሎች ሰብሎች ላይ እሴት በመጨመርና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት እንደሚያስችል እንዲሁ። በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች መሰል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደስራ ገብተዋል። ከነዚህም መካከል በሀዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማና  በኮምቦልቻ የተገነቡት ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም