የህግ የበላይነትን ለማስከበር የፍትህና ዴሞክራሲ ተቋማት ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለፀ

77
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ የፍትህና ዴሞክራሲ ተቋማት አሰራርና አደረጃጀታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለፀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ጋር ትውውቅና የ100 ቀን እቅድ አድምጧል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሀገሪቱን የፍትህ ስርዓት በማጠናከር የዜጎችን ህገ መንግስታዊና ህጋዊ መብቶችን ማስከበር ይገባል። የዜጎችን ህገ መንግስታዊና ህጋዊ መብቶችን ለማስከበር የፍትህና ዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ጉልህ ድርሻ አላቸው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በሀገሪቷ እየታዩ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ ለማድረግና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተቋማቱ ተጠናክረው መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ለዚህም ተቋማቱ ከሰራተኞች ምደባ በተጨማሪ አሰራርና አደረጃጀታቸውን መፈተሽና ኀብረተሰቡ የሚጠብቀውን አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱም አሳስበዋል። የዛሬው መድረክም የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የተቋማቱ አመራሮች ትውውቅ የሚያደርጉበትና የተቋማቱ የ100 ቀን እቅድ የሚደመጥበት እንዲሁም የቀጣይ ግንኙነት አግባብ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ለመነጋገር ያለመ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ "የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ መስራት አለባቸው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ አቤል አዳሙ ናቸው። በተለይ መገናኛ ብዙሃን ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ አቤል ፍርድ ቤቶችም ሰዎች ሳይጉላሉ በህግ አግባብ ብቻ የሚዳኙበትን መንገድ ማመቻቸት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም