በብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ

47
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 በመጀመሪያው የ2011 ዓ.ም ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። በድሬዳዋ አዘጋጅነት ከትናንት በስቲያ የተጀመረው ውድደር ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል። ዛሬ በ54 ኪሎ ግራም ሴቶች የአዲስ አበባ ፖሊሷ ገነት ጸጋዬ ከድሬዳዋ ከነማዋ ኤልሳቤት ብርሃኑ ጋር የፍጻሜ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የውድድርና ስልጠና ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። በ81 ኪሎ ግራም ወንዶች የማራቶኑ ገዛኽኝ ሮባ ከፌዴራል ፖሊሱ አብዱልፈታ ከሚል፣ በ91 ኪሎ ግራም ወንዶች የድሬዳዋ ከነማው ግርማ አበበ ከፌዴራል ፖሊሱ ሙሉቀን መልኬ ጋር የወርቅ ሜዳሊያውን ለማግኘት ይጫወታሉ። ከፍጻሜ ጨዋታዎቹ በተጨማሪ በ49፣ 60 እና በ64 ኪሎ ግራም ወንዶች ለፍጻሜ ለማለፍ የሚደረጉ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ከትናንት በስቲያ ውድድሩ ሲጀመር ከ91 ኪሎ ግራም በላይ የወንዶች የፍጻሜ ጨዋታ የድሬዳዋ ከነማው ሊበን መሐመድ የፌዴራል ፖሊሱን አዲሱ ሁንዴሳን በማሸነፍ የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። የመጀመሪያው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድሩ ነገ ይጠናቀቃል። ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ቀሪዎቹ ውድድሮች በወላይታ፣ ጅግጅጋና አዲስ አበባ ይካሄዳሉ።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም