በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በግጭት የተጠረጠሩ 53 ግለሰቦች ተያዙ

125
ጎንደር ህዳር 28/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ፤ በምስራቅና ምእራብ ደንቢያ ወረዳዎች ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው ግጭት ወደ መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የግጭቱ ዋነኛ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 53 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ሲውሉ 29 የጦር መሳሪዎች መያዛቸውም ተገልጿል። የመምሪያው ሃላፊ ኮማንደር እንየው ዘውዴ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የፀጥታ መዋቅሩ ከሀይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት ግጭቶቹን መቆጣጠር ተችሏል፡፡ “በአሁኑ ወቅት በአካባቢዎቹ ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ ነው” ያሉት ሃላፊው ህብረተሰቡ አብሮ የመኖር ባህሉንና እሴቱን በመጠበቅ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የጸጥታ መዋቅሩ የአካባቢውን ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የግጭቱ ጠንሳሽና ተዋናይ ነበሩ የተባሉ 53 ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በአሁኑ ወቅት ህግ ፊት ለማቅረብ አስፈላጊውን መረጃ የማጠናቀር ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። በግጭቱ ታሳታፊ ከነበሩ ግለሰቦችም 29 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን የጠቆሙት ኮማንድሩ 490 የተለያዩ ጥይቶችና 18 የጥይት ሳጥኖች በጸጥታ ሃይሉ እጅ መግባታቸውን ገልጸዋል። እንደ ኮማንደሩ መግለጫ በግጭቶቹ ምክንያት በርካታ ዜጎች የህይወትና የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል። የጸጥታ ሃይሉ ህግ የማስከበር ተልእኮውን አጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ኮማንደሩ የሰላሙ ባለቤት ህዝቡ እራሱ በመሆኑ የጀመረውን የተቀናጀ ጥረት እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም