በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታትና የተፈናቀሉትን ለመርዳት መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ተባለ

77
አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታትና ህዝቡ ወደሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ መንግስት ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ገለፁ። በክልሉ የሚታዩ ግጭቶችን ለመከላከልና ሰላምን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር /ኦነግ/ እና ኦሮሞ ፌዴራልስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ ከኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና ከኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ጋር በመሆን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። መግለጫው ከሰሞኑ በቤንሻንጉልና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ላይ ያተኮረ ነው። በግጭቱ የኦሮሚያ ፖሊሲን ጨምሮ  ሌሎች ንፁሃን ሰዎች ሞተዋል፤ በርካቶች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ክስተቱ እንዳሳዘናቸው የተናገሩት አቶ ለማ፤ "ግጭቱን ለማርገብ በፍጥነት አልደረሳችሁልንም በሚል ከህዝቡ እየተሰማ ያለው ቅሬታም ተገቢ ነው" በማለት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በየአከባቢው የሚከሰተው "ሞትና መፈናቀል ይቁምልን" በሚል እየተደረጉ ያሉ ሰላማዊ ሰልፎችም ተገቢ ናቸው ብለዋል። ሆኖም ግን በዚህ ውስጥ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት ጥፋት እንዳይፈፅሙ ህዝቡ ነቅቶ መከላከልና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል። "በአሁኑ ወቅት የሚታየው ይህ ችግር ለኦሮሞና ኦሮሚያ ክልል የተለየ አጀንዳ በመፍጠር ያሻቸውን መስራት የሚፈልጉ ሃይሎች እኩይ ተግባር አካል ነው" ሲሉም አቶ ለማ ገልፀዋል። የአሁኑ ከስተት ባለፉት ጊዜያት በምስራቅ አሮሚያና ሶማሌ አካባቢ እንደዚሁም በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ውስጥ ከተከሰቱት ህዝብን የማጋጨት ተግባር ጋር የሚመሳሰል ባህሪ እንዳለው ጠቅሰዋል። የክልሉ መንግስት የፌዴራል መንግስትን እርዳታ በመጠየቅ ጭምር ግጭቱን ሙሉ በሙሉ ለማስቆምና የተፈናቀሉትን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት መጀመራቸውን አቶ ለማ አስታውቀዋል። ግድያንና ማፈናቀልን ጨምሮ ሆን ብለወ በህዝቡ ላይ ግፍ የፈጸሙ አካላት ህግ ፊት እንዲቀርቡም መንግስት  እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ጠቅሰው በዚህም ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ካለመቀራረብና መናበብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመድፈን መንግስታቸው ከፓርቲዎቹ ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑንም አቶ ለማ ገልጸዋል። መንግስት በነዚህ አካላት ላይ የሚወስደው እርምጃ ጠንካራ እንደሚሆን በመግለጽ ህዝቡ ግጭቶቹ የሌላ ጥቅም ፈላጊ ሴረኞች ተግባር መሆኑን በመገዝብ ኦሮሚያ ወደሰላሟ እንድትመለስ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የክልሉ ፕሬዚዳንት ጥሪ አቅርበዋል። የኦነጉ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው የተፈጠረው ግጭት በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሮ ለበዙሃን ተስፋ የሰጠውን የለውጥ እንቅስቃሴ የማደናቀፍ ሴራ ነው ብለዋል። የወሰን ጉዳይ በማስመሰል የሚስተዋለው ይህ ክስተት ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጨት ዓላማ ያላቸው አካላት እጅ እንዳለበት እናምናለን ሲሉም የኦነጉ መሪ ገልፀዋል። በግጭቱ ምክንያት በጠፋው ህይወትና መፈናቀል የተሰማቸውን ሃዘን የገለፁት አቶ ዳውድ "ወደፊትም ሆነ አሁን የተጀመረውን ለውጥ ማደናቀፍ አይቻልም፤ እንዲህ ዓይነት ጥረቶችን ለመከላከልም ከመንግስት ጋር በጋራ እንሰራለን" ብለዋል። የህዝብን ጥቅም የሚጋፋ ማንኛውንም አይነት ተግባር ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። "መንግስታና ህዝቡን እወክላለው የሚል ፖሊቲከኛ የህዝቡን ዳር ድንበር ብሎም ሰላሙን መጠበቅ ግድ ይለዋል" ያሉት ደግሞ ዶክተር መረራ ናቸው። ህዝቡ  የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ኦሮሞን ወክሎ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና ምሁራን እየተጉ መሆኑን የገለፁት ዶክተር መረራ ይህንን እውን ለማድረግ በግልም ሆነ በፓርቲ ደረጃ የበኩላቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም