በመዲናዋ አዘጋጅነት የሚካሄደው 13ተኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዋዜማው በደማቁ እየተከበረ ነው

129
አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 በመዲናዋ አዘጋጅነት የሚካሄደው 13ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዋዜማው በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት  እየተከበረ ይገኛል። በዓሉን በማስመልከትም ዛሬ ''ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ '' በሚል ሀሳብ ከ76ቱም ብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት መረሃ ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሄዷል። ኢትዮጵያዊ መገለጫችን የሆነው ቡና ለመሰባሰብ፣ ለመወያየትና ለእርቅ የምንገናኝበት፤ ጥንትም የነበረ ባህላችን ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለህብረብሄራዊ በዓላችን ማድመቂያና ማስተሳሰሪያ ስላስፈለገን በጋራ ይጠጣል ተብሏል። በዓሉን የአገር ሽማግሌዎች በምርቃትና ስለ አገር ሰላም ጸልየው ከፍተዋል። በዓሉን በማስመልከትም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ  ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔና  የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ለታዳሚዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን ኪዳኔ በመልዕክታቸውም፣ ቡና በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚበቅልና የሚያድግ ባይሆንም ግን ቡና የሁላችን የኢትጵያኖች የአንድነት መገለጫ ነው። በዓሉን ስናከብርም የአንድነት መንፈስ ይዘን እንድንጓዝ  ዛሬ አንድ ላይ መሰባሰባችን ትልቅ እድል የሚፈጥርልን ነው ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው፣ ከምንም በላይ ይህን በዓል በአይነቱ ለየት የሚያደርገው  ከወትሮው በበለጠ መቻቻልንና እርቅን መነሻ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ዓለማ ተደርጎ እየተከበረ በመሆኑ ነው ብለዋል። አንዲት ያደገች ያማረችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ከመፍጠር አኳያም በአንድነት ጎልብተን እንድንሰራ የሚመክር መድረክ ነው በማለት  አፈ ጉባኤዋ አክለዋል። ዛሬ በበዓሉ የታደሙት የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ልጆች ፣ በስፍራው እርስ በእርስ የመተዋወቅና በጋራ የመወያየት እድል በማግኘት በጋራ አዚመዋል። ኢትዮጵያዊ ባህሉን የጠበቀ በደማቅ ስነስርዓት የተዘጋጀውን ቡና በአንድነት ቁጭ ብለው ጠጥተዋል። የፊታችን ቅዳሜ ህዳር 29 የሚከበረውን በዓልም በደመቀ መልኩ ለማክበር፣ ፍቅርና አንድነትን ለመስበክ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው በአደባባይ ስለ አንድነት ለመዘመር ዝግጅታቸውን አንዳጠናቀቁና በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑንም የበዓሉ ታዳሚዎች ገልጸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም