ፓርቲዎቹ በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል አብረን እንሰራለን አሉ

89
አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 በአገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ያላቸው የሃሳብና የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው በጋራ  እንደሚሰሩ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አረጋገጡ። ፓርቲዎቹ በጋራ ጉዳይ ላይ አብረው የሚሰሩበት የጋራ ፎረምም ለማቋቋም ተስማምተዋል። ገዢው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ጨምሮ በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዛሬው ዕለት አባ ገዳዎች የሃይማኖት አባቶች፣ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ምሁራን በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳዮችና የወደፊት ግንኙነታቸው ላይ በአዲስ አበባ መክረዋል። "ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግርና የኦሮሚያ ወቅታዊ ሁኔታ" የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ውይይት፣ በኦዴፓ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋና የፖለቲካ ምሁሩ ፕሮፈሰር እስቅኤል ገብሳ  ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ ነበር የተጀመረው። በጽሁፋቸውም በቅርብ አመታት በክልሉ ለአገራዊ ለውጥ ጭምር መነሻ የሆነ ለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴዎች እንደ ነበሩ በማስታወስ በተደረገው ዋጋ ያስከፈለ ትግልም አያሌ ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የገለጹት። ሆኖም ግን ዛሬም ድረስ ክልሉ ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውና ይህ ለውጥ የሚያስፈራቸው አካላት ለውጡን ለመቀልበስ 'እልህ አስጨራሽ ትግል'' እያደረጉ መሆኑ እንደ አሳሳቢ ተግዳሮት ተጠቅሷል። በየአከባቢው የሚንጸባረቁ ግጭቶች ሞትና መፈናቀሎች እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚታዩ የመንጋ ፍትህና ህገ ወጥነትን ለአብነት በመጥቀስ። በመሆኑም ለዚህ ትልቁ መፍትሄ ያሉት የብሄሩን ጥቅም አስከብራለሁ ብሎ በኦሮሞ ስም  የተደራጀ  የፖለቲካ ፓርቲ አብሮና ተቀናጅቶ መስራት የሚል ሃሳብ አቅርበዋል። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ውይይት ያደረጉት ፖለቲከኞቹም ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ኦሮሚያ ላይ የተለየ ትኩረት አድርጎ እየሄደ መሆኑን አውስተዋል። ለውጡ ደግሞ እንደ ኦሮሞ ህዝብም ሆነ እንደ አገር አስፈላጊ በመሆኑ ማስቀጠሉን የህልውና ጉዳይ አድርገው እንደሚሰሩበትም ተግባብተዋል። ከነዚህ መካከል የኦነጉ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እንዳሉት "ለውጡን ዋጋ በከፈለበት ሰፊው ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት መቆም አለበት፤ የሚጠየቀውም ጥያቄ በአፋጣኝ መልስ ማግኘት አለበት" ብለዋል። ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚሰራ የተባለውንም አካል መንግስት በአፋጣኝ ለይቶ ለህዝቡ ይፋ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል። ለውጡ ደግሞ ለሁሉም አስፈላጊ በመሆኑ ከሁሉም ይመለከተኛል ከሚል አካል ጋር ተባብሮ ለማስቀጠል ያላቸውን ዝግጁነትንም አረጋግጠዋል አቶ ዳውድ። የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው፣ 'ነጻ ወጣን ማለቱና አዋቂና መሪ ነን'  ማለቱ የህዝብን ሰቆቃ ካላቆመና በአገር ላይ ተረጋግቶ የመኖር ዋስትና ካልሰጠ "ከንቱ መሆኑን" ነው ያነሱት። በፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነትና በፖለቲካ ጨዋታ ህዝብ መጉዳት እንደማይገባም በማሳሰብ ለውጡን ማስቀጠል የጋራ አጀንዳቸው መሆኑንና ለዚህም ተረባርቦ ወደ ፊት ማስካሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል። በመድረኩ የተሳተፉና ሃሳበቸውን የገለጹት ሌሎች ፓርቲዎችም ለውጡን ማስቀጠል ላይ ሁሉም በትብብር መስራት ይገባል የሚል ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ይዘው ነው የተለያዩት። በመድረኩ የተሳተፉ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶችም ብሄሩን ወክለው የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች ለጊዜው የመፎካከርን ስሜት ወደ ጎን አድርገው ህዝቡ የጓጓለትን ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴ መሰረት ማስያዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ይህን ለማድረግም የፓርቲዎች መሰባሰብና ቁጥራቸውን መቀነስ ብሎም አገራዊና ክልላዊ ጉዳይ ላይ የሚመክሩበት ቋሚ መድረክ መፍጠር በመድረኩ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ነበሩ። ለዚህም የጋራ ፎረም ማቋቋምና ሁሉም የሚገዛበት የስነ ምግባር መመሪያ ማዘጋጀት ይገባል ተብሎ በጽሁፍ አቅራቢዎች የተነሳውንና በአቶ ጀዋር መሃመድ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይም ተቀባይነት አግኝተዋል። በዚህም በቅርብ ቀን ውስጥ መነሻ ሃሳብ በምሁራን ቀርቦና ተመክሮበት የጋራ ፎረም አንዲቋቋም ተወስኗል። በመድረኩ የተገኙ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ህዝቡ የከፈለውን ዋጋ የሚመጥን ጥቅም ማግኘት ሲገባው ዛሬም ድረስ ህዝብን ሰላም የሚያሳጡ ክስተቶች መቀጠላቸው እንደሚያሳስባቸው ነው የገለጹት። አሁን የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ መሆኑንም ሁሉም መገንዘብ እንደሚገባው ያሳሰቡት አቶ ለማ በአሁኑ ወቅትም "የምንተቻቸበትና የምንፎካከርበት ሳይሆን አገር የሚናድንበት ነው" ብለዋል። በመሆኑም ህዝቡም ሆነ ፓርቲዎች በተለየ የሃላፊነት ስሜት ተባብረው መስራት ግዴታቸው መሆኑን አጽንተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም