አብዴፓ 72 አመራሮቹንና አባላቱን በክበር አሰናበተ

79
ሰመራ ህዳር 27/2011 የአፋር ብሄራዊ ዴሞከራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ 20 ነባር አመራሮችን ጨምሮ 72 አባላቱን በክብር አሰናበተ፡፡ ከተሰናባቾቹ መካከል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲው ሊቀመንብር አቶ ስዩም አወልና ሌሎች የስራ አስፈጻሚና ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ይገኙበታል፡፡ የጉባኤው ፐሬዚዲየም ሰብሳቢ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃደር እንደገለፁት ተሰናባቾቹ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራርነት ያገለገሉ፣ በ1992 አብዴፓ ሲመሰረትም አባል የነበሩና እስካሁንም በኃላፊነት እያገለገሉ ያሉ ናቸው። በአመራርነት ቦታ በነበራቸው ቆይታ የአፋርን ህዝብ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድርግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በፓርቲው አባላት ሰም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በክብር ከተሰናበቱት መካከል የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ስዩም አወል በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በተሻለ ብቃት ፓርቲውንና ክልሉን ሊመሩ የሚችሉ ወጣቶች ወደ አመራርነት ማምጣት የወቅቱ ጥያቄ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆነም ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው በመልቀቅ ለአዲሱ ትውልድ ስልጣናቸውን በክብር ለማስረከበር በመብቃታቸው ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በክልሉ በተመደቡበት የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ለአፋር ህዝብ የልማት ተጠቃሚነትና ለዴሞክራሲ መጎለበት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በአመራርነት ዘመናቸው ለተሰሩ ለስህተቶች የክልሉ ህዝብና መሪ ድረጅታቸውን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን በቀጣይ ከፓርቲው አዲስ አመራሮችና ከክልሉ ህዝብ ጎን በመቆም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አንደሚደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ በክበር የተሰናበቱት አባላትም የአብዴፓ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ስዩም አወል፤ የፖርቲው ስራ አስፈፃሚ የነበሩ አቶ እስማኤል አሊሴሮ፣ አቶ ኡስማን አኒሳ፣ አቶ መሃመድ አላሌ፣ አቶ ኤልያስ ሀሰን እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ የፖርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩት አቶ አሊ አብደላ፣አቶ መሃመድ አቡበክር፣ አቶ አሎ አፍኬኤ፣ አቶ መሃመድ ቦልኮ፣ ወይዘሮ ዘሃራ መሃመድ፣ አቶ ኡስማን መቅቡል፣ አቶ መሃመድ ያዩ፣ አቶ ኡስማን መሃመድ ከንዴ፣ አቶ ሙሳ ማህሙዳ በክብር የተሰናበቱት አመራሮች ናቸው በተጨማሪም የፖርቲው ኦዲት ኮሚቴ አባላት የነበሩ አቶ መሃመድ ጣሂሮ፣ አቶ እድሪስ ኪያርና አቶ አልዩ ሽፋ እንዲሁም የፖርቲው መስራች አባላት የነበሩ አቶ መሃመድ ቦልኮ፣ ወይዘሮ መዲና ማህሙድና አቶ አወል ወግሪስ ከፖርቲው በክብር ተሰናብተዋል፡፡ የተጠቀሱትን 20ዎቹን ጨምሮ ፓርቲው በአጠቃላይ በክብር ያሰናበታቸው አባላቱ ቁጥር 72 መሆናቸው ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም