ልዩነቶችን አቻችሎ በሰላምና በፍቅር የመኖር እሴት ሊጠናከር ይገባል

89
አዲስ አበባ  ህዳር 27/2011 የኢትዮጵያ ልዩነቶችን አቻችሎ በሰላምና በፍቅር የመኖር የቆየ እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው ዜጋ የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት ተባለ። ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን በጋራ የመኖር ባህል እንዳይሸረሸር በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸውም ተገልጿል። ይህ የተገለፀው በመጪው ቅዳሜ የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ክብረ በዓል ጋር በተያያዘ ዛሬ በተከናወነው ደማቅ የቡና መጠጣት ስነ-ስርዓትን ለመታደም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተገኙ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ነው። በዚሁ አስከ 10 ሺህ የሚደርስ ህዝብ በታደመው የቡና መጠጣት ስነ-ስርዓት ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በአገሪቱ በተለይ ብሄር ተኮር የሆኑ አስተሳሰቦችንና ችግሮችን በማስወገድ አንድነትን ማጠናከር ይገባል። የዛሬው የቡና መጠጣት ስርዓትም የኢትዮጵያዊያን አንድነትና መተሳሰብ የቆየ ባህላዊ እሴት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ከአላባ ዞን የመጡት አቶ አህመድ መሶሮ "በአሉ በዚህ መልኩ መከበሩ ሁሉም ብሄረሰብ በአንድ ጀበና መጠጣቱ ለሰላም  ይጠቅማል ብዬ ነው ማስበው፤ አገራዊ አንድነትን የሚፈጥር ነው ቡና በአንድ ላይ መጠጣቱ ሁሉም የየራሱን የባህል አልባሳት ለብሶ አንድ ላይ መጠጣቱ አንድነትን ይገልጻል።" "ለሰላም ኑ ቡና እንጠጣ የሚለው ፕሮግራም በጣም የተለየ ነው እኛ በባህላችን በኢትዮጵያዊነታችን ቡና ለለቅሶ፣ ለእርቅ፣ ሰው ለመጠየቅና ለሌሎችም ይጠጣል ይህም ብዙ ነገራችንን ስለሚገልጽልን የዘንድሮ ፕሮግራም የተለየ ያደርገዋል ብዬ ነው የማስበው" ያሉት ደሞ ከጉራጌ ዞን የመጡት ወይዘሮ ባህሯ ዴንኬሮ አንድ ቤት አለችን እሷም "ኢትዮጵያ ናት" ለዚህችም አገራችን ተባብረንና ተፈቃቅረን ለሰላሟ፣ ለእድገቷ፣ ለልማቷና ለአንድነቷ ዘብ በመቆም የበለጸገች ኢትዮጵያን መፍጠር ይገባልም በማለት ተናግረዋል። 13ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን "በብዘሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ አዘጋጅነት ህዳር 29 ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም