በክልሎች መካከል ላለው ግንኙነት ቻርተር እየተዘጋጀ ነው

551

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የግንኙነት ቻርተር ሥራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።

በህዝቦች መካከል የበለጠ መቀራረብ እንዲፈጠር በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።

ምክር ቤቱ እንዳመለከተው ቻርተሩ ክልሎች በልማት እንዲተሳሰሩ፣ የሚገጥሙ አለመግባባቶች ሰላማዊ እሴትን በጠበቀ መልኩ እልባት እንዲገኝላቸው፣ የተሞክሮ ልውውጥ እንዲያደርጉ ማዕቀፍ መዘርጋትን ያካተተ ነው።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የሕገ-መንግሥት አስተምህሮትና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊ  ወይዘሪት ፍሬወይኒ ገብረእግዚአብሄር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እየሰራ ነው።

በተለይ ህዝቦችን የሚያቀራርቡ ስልቶችን በጥናት በማስደገፍ  እየተሰሩ ነው ያሉት ጸሃፊዋ አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚያጎለብቱ አገር አቀፍ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

ከውይይቱ ጎን ለጎንም በክልሎች መካከል ዘላቂነት ያለው ትስስር እንዲፈጠር የሚያግዝ ቻርተር መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

እንደ ወይዘሪት ፍሬወይኒ ገለጻ የቻርተሩ የመጀመሪያው ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለክልሎች ተልኳል፤ የሚሰጡትንም ሀሳብ በማካተት በተያዘው ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው።

ቻርተሩ የመንግሥታት ግንኙነት መዕቀፍን መነሻ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቻርተሩ ሕግ አውጪዎች፣ አፈጉባኤዎችና አስፈጻሚዎች ግንኙነት የሚፈጥሩበት አሰራር እንደሚኖረው ጠቁመው በጤናው፣ በትምህርት፣ በግብርና የጸጥታ አካላት የሚያቀናጅ መሆኑም አስረድተዋል።

”ዑጋዞች፣ የሃይማኖት አባቶች በዓመት ሁለት ግዜ እየተገናኙ የአካባቢያቸውን ሁኔታ እየገመገሙ አቅጣጫ እያስቀመጡ ችግሮችም ካሉ ቁጭ ብለው እዚያው እያረሙ እየፈቱ የሚሄዱበት ስርዓት እንዲኖርም ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

በተለይ አምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች ታህሳስ የመጀመሪያው ሳምንት የሚመለከታቸው አካላት በሚገኙበት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

እንደ ወይዘሪት ፍሬወይኒ ገለጻ ቻርተሩ ሥራ ላይ ሲውል ህዝቦችን ከማቀራረብ ባሻገር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዞ ማሳካት የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።