የመንግስት ተቋማት አሰራራቸውን ወረቀት አልባ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል

1923

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የፌደራል መንግስት ተቋማት በወረቀት የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመተካት ከወረቀት የፀዳ አሰራር ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገለፀ።

በተለምዶ በወረቀት የሚከናወኑ ተግባራት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ለጥፋት ከመዳረግ ባሻገር የተንዛዛ አሰራርን በመፍጠር የአገልግሎት ጥራትን እንደሚያስተጓጉል የብዙዎች አስተያየት ነው።

ይህንን ጊዜ ያለፈበት አሰራር በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ወረቀት አልባ የአሰራር ስርዓትን መፍጠር እነዚህን ችግሮች እንደሚፈታ ነው ስርዓቱን መተግበር የጀመሩ ተቋማት ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ከወረቀት የፀዳ አሰራር፤ ሰነዶችን ከጥፋት እንደሚታደግ፤ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልገሎት ለመስጠት ብሎም አመቺ የሥራ ድባብ ለመፍጠር እንደሚያስችል ኢዜአ ያነጋገራቸው እነዚሁ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ከፊል አሰራራቸውን ወረቀት አልባ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የሚገልፁት ባለሙያዎቹ በአስካሁኑ ትግበራቸውም በርካታ የአሰራር ጥራትንና ፍጥነትን ጨምሮ ሌሎች ጠቀሜታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥም አሰራራቸውን ሙሉ በሙሉ ከወረቀት የፀዳ ለማድረግ አቅደው በመሥራት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በኢትዮ-ቴሌኮም የስትራቴጂና ፕሮግራም ማኔጅመንት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሀዲ ጀማል እንደገለጹት ከአጠቃላይ የተቋማቸው አሰራር ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከወረቀት የፀዳ እንዲሆን ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ከሚገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮ-ቴሌኮም ሰራተኞች ጋር የሚደረገው የእለት ተእለት ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ከወረቀት የፀዳ መሆኑን አቶ መህዲ አንስተዋል።

ቁልፍ ከሆኑት የተቋሙ የሥራ ክፍሎች መካከል የሆነው ግዢና የፋይናንስም አሰራር ከወረቀት የፀዳ እንዲሆኑ እየተደረጉ ካሉት ክፍሎች መካከል እንደሆነም ገልፀዋል።

ይህም የተቋሙ አጠቃላይ እንቅስቃሴን ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማጠናከር እንደዚሁም የጊዜና ወጪ ብክነትን ለመቀነስ እያስቻለ መሆኑም  ተረጋግጧል ብለዋል።

በቀጣይም ፕሮጀክት ማኔጅመንት ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ የሚያደርግ በአገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል የሚሆን አሰራር ለመተግበር  ኢትዮ-ቴሌኮም ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ባለሙያ አቶ መሀዲ ጀማል ጠቅሰዋል።

ተቋሙ ከሶስተኛ ወገን ጋር የሚያያይዘውን ተግባርም ወረቀት አልባ (በአውቶሜሽን የተደገፈ) ለማድረግም እየሰራ ነው ብለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፍ የሪፎርምና መልካም አስተዳደር ባለሙያ አቶ መኮንን ይሄይስ በበኩላቸው በወረቀት የሚከናወኑ ተግባራትን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የመለወጡ ስርዓት በሁሉም የሚኒስቴሩ መዋቅሮች ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል።

ይህም ከላይ እስከታች ባሉት መዋቅሮች መካከል ቀልጣፋና ጥራት ያለው መረጃ በመለዋወጥ፤ ተናቦ ለመስራትና ውጤታማ የክትትል አሰራር ለመዘርጋት እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል።

ወረቀት አልባ በሆነ መንገድ የተዘረጋው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓቱ ኃላፊዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ጭምር በየትኛው ቦታና ጊዜ የስራ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት ለመከታተል እንዳስቻላቸውም አክለዋል።

ይህም አገልግሎቱን ቀልጣፋ ከማድረግ ባሻገር ተዓማኒነት ያለው መረጃ ለመስጠት አግዟል ሲሉም ገልጸዋል።

በቀድሞ የኮንስትራክሸን ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኘነት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሲሳይ ደርቤ ሚኒስቴሩ ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር ሳይዋሃድ በፊት ወረቀት አልባ አሰራር ተግባራዊ ለማድርግ ዝግጅት ማድረጉና በሙከራ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

መረጃዎችን የመለየት፣ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ ሶፍት ዌር የማልማትና ግብዓቶችን የማሟላት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር መዋሃዱ ዘርፉን የሚያሰፋ በመሆኑ የአወቶሜሽን ሰራው ተጠናከሮ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።