ዛሬ በጋራ የጠጣነው ቡና አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናክር ችግሮቻችንን የምንፈታበትን ሰፊ አጋጣሚ ነው-የበዓሉ ተሳታፊዎች

1445

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 ዛሬ በጋራ የጠጣነው ቡና አንድነታችንን ይበልጥ የሚያጠናክርና ችግሮቻችንን የምንፈታበት ሰፊ አጋጣሚ እንደሚፈጥር የብሄር  ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ተወካዮች ገለጹ።

13ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ምክንያት በማድረግ 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ዛሬ በመስቀል አደባባይ ቡና ጠጡ ፕሮግራም ላይ ታድመዋል።

”ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ” በሚል የተዘጋጀው ይህ መረሃ ግብር ከ76  ብሄሮችና ብሄረሰቦች የተወከሉ ታዳሚዎች የተሳተፉበት ሲሆን በፕሮግራሙ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈውበታል።

በፕሮግራሙም ታዳሚዎቹ በጋራ ቡና እየጠጡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት መክረዋል፤ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መወያየት መፍትሄ በመሆኑ የነበረውን ባህላችንን አጠናክረን በመቀጠል ለጋራ ሰላማችን መፍትሄ ለማበጀት እንሰራለንም ብለዋል።

አቶ ፈድሉ ኪያር ከደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ የቀቤና ማህበረሰብ ተወካይ  እንዳሉት“ብዙ ሆነሽ አንድ ቦታ ላይ ተገኝተሽ ስለ አንድ አገር የምትወያዪበት እድል የፈጠረ ነው።” ይህም አንዳንድ ቦታዎች  ከለውጡ ጋር የሚታዩ የተለያዩ ነገሮች ተወያይቶ ለአገራችን የጋራ መፍትሄው መስጠትም ያስችላል፡፡

ወይዘሪት ፋጡማ ሁሴን ከአፋር ክልል ሰመራ የመጣች ሲሆን ቡና በተለይ በኢትዮጵያ በአንድነት ተሰባስበን የምንጠጣው በመሆኑ ስለ ሰላማችንና ስለአንድነታችን  የምንወያይበት ነው ብላለች።

 ወይዘሮ ማስረሻ ንጉሴ ከአዲስ አበባ  የበዓሉ ታዳሚ በመሆን ተገኝተዋል። ይህ አይነቱ ፕሮግራም መዘጋጀቱ መልካም ነው በማለት፣ ቡና ድሮም እናቶቻችንና አባቶቻችን ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይጠቀሙበታል እኛም ለልጆቻችን ይሄንኑ ማስተማር አለብን ብለዋል።

 አቶ አራጌ ይማም ከአማራ ክልል ደሴ ከተማ የመጡ ሲሆን ከድሮም እየተሰባስበን ችግሮቻችንን የምንፈታው በቡና ነው፤ ቡና አሁንም ለሰላማችን መስፈን ተሰባስበን የምንወያየው የምንገናኘው በቡና በመሆኑ የአንድነታችን ማሳረጊያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነት በብዙዎች ውስጥ አንድ ሆና የምትደምቅ አገር በመሆኗ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል ተጠናክረን ስለአንድነታችን ስለ ሰላማችን ተግተን እንሰራለን፣ ወደ መጣንበት ስንመለስም ብዝሃነታችንን ለማስጠበቅ ተግተን እንሰራለን ነው ያሉት ታዳሚዎቹ።

13ተኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በአፍሪካ መዲና በአዲስ አበባ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን የዛሬው ፕሮግራም

”ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ” በሚል የተከበረው የበዓሉ አንዱ መረሃ ግብር ነው።

አዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫ እግዶቿን እየተቀበለች ትገኛለች፣ በምሉም የፊታችን ቅዳሜ ”በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ  በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።