የአለልቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሰልጣኝ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ምርት ሰበሰቡ

85
አለልቱ ህዳር 26/2011 የአለልቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሰልጣኝ ማረሚያ ቤት ፖሊሶች የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ምርት ሰበሰቡ። የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር የሚገኘው የአለልቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አመራሮች፣ ሰራተኞችና ሰልጣኝ ማረሚያ ቤት ፖሊሶች በኦሮሚያ ክልል አልለቱ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ምርት ሰብስቧል። ፖሊሶች ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ ህብረተሰቡን የማገዝ ተግባር ማከናወናቸው እንዳስደሰታቸው ምርታቸው የተሰበሰበላቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል። ፖሊሶች ከሰላም ማስከበርና መደበኛ ስራቸው በተጨማሪ በዚህ መልኩ የጋዟቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ገለጸው ከወጪ እንደታደጋቸውም አመልክተዋል። አርሶ አደር እንግዳወርቅ ጌታቸው እንደተናገሩት"መንግስት ከጎናችን ሆኖ እነዚህ ፖሊሶች በሰላምም፤ በ ማንኛውም ነገር ከጎናችን ሆነው ሲያገለግሉን የቆዩ ናቸው፣ወደፊትም የሚያገለግሉን ናቸው።አሁን ደግሞ ወደኋላ የቀር አቅመ ደካማ ቤተሰብ ለማስተዳደር ለባተለ ሰው በመርዳታቸው በጣም ደስ ብሎኛል። እሰከአሁን የተሰራልኝ ስራ በቀን ስራተኞች ቢሰራ 2 ሺህ ብር ይሆናል፣በጣም ነው የማመሰግነው"። "ትብብሩ በጣም ደስ የሚል ነው፤ ጦሩ እንደዚህ ወጥቶ አዝመራቸው ወደኋላ የቀሩትን ደካሞችን  ማገዙ በአሁኑ መንግስት በጣም ትብብር አግኝተናል፣ደስ ብሎናል” ያሉት ደግሞ አርሶ አደር በቃሉ ጎሽሜ ናቸው፡፡ የአርሶ አደሮችን ምርት ስብሰባ ላይ የነበሩ የአለልቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሰልጣኝ መኮንኖች በበኩላቸው ከስልጠናቸው በተጨማሪ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማገዝ ማህበሰባዊ ግዴታ ለመወጣት በፍቃዳቸው እንደመጡ ተናግረዋል። ከህብረተሰቡ የወጡ በመሆናቸው ህብረተሰቡን የማገዝ ግዴታ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። "ከስልጠናው በተጨማሪ ማህበረሰቡን መርዳት በአስተማሪያዎቻችንም ሆነ በኛም ፍላጎት በመነሳሳት ነው” ያሉት  እጩ መኮንን አዘናጋቸው አጥናፍ ናቸው፡፡ አክለውም  ህብረተሰቡ ከኛ ጎን ስለሆነ እኛም ከህብረተሰቡ ጎን ስለሆንን አቅም ደካሞችን ማገዝና በማንኛውም ጊዜ  መረዳዳት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ እጩ መኮንን ሀብታሙ ጥላሁን በበኩላቸው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጥቶ ሰብሉን እንዳያበላሽ እኛም ህብረተሰቡን ማገዝ አለብን በሚል ወደ 227 የሚደርሱ እጩ መኮንኖች በአጨዳው ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው በቀጣይም እንሰራለን ብለዋል፡፡ በአለልቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመስክ ስልጠና ቡድን መሪ የሆኑት ምክትል ኦፊሰር አበባው ካሳ ሰልጣኙ ከህብረተሰቡ የወጣ በመሆኑ የህብረተሰብ አገልጋይ መሆኑን በተለያዩ በጎ አድራጎት ላይ በመሳተፍ አጋርነቱን እየገለጸ መሆኑን ተናግረዋል። የአለልቱ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በ1970 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን እስከአሁን ከ20 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን በተለያዩ የስልጠና አይነቶች አሰልጥኖ አስመርቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም