ፍላጎታቸውን ያላሳወቁ የመንግስት ባለ በጀት ተቋማት ዕቃ አቅራቢ አይመደብላቸውም

61
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የግዥ ፍላጎታቸውን ያላሳወቁ የመንግስት ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች እቃ አቅራቢ ድርጅት አይመደብላቸውም ተባለ። ፍላጎታቸውን ያላሳወቁ ተቋማት በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ዕቃ አቅራቢዎች የማይመደብላቸው መሆኑን ያስታወቀው የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ነው። የመንግስት ባለ በጀት ተቋማት ለሶስት ዓመታት የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ ዕቃዎች ዝርዝር እስከ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ለአገልግሎቱ ማሳወቅ ነበረባቸው። ይሁንና ከ142 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ፍላጎታቸውን በወቅቱ ያሳወቁት 82 ብቻ ሲሆኑ ከ45 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ 22 ናቸው። አገልግሎቱ ዛሬ ከ2011-2013 በጀት ዓመት ስለሚያከናውነው የማዕቀፍና የስትራቴጂክ ግዥና ንብረት ማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ባደረገው ውይይት የተሳተፉና ፍላጎታቸውን በጊዜ ያላሳወቁ ተቋማት ተወካዮች 'ውሳኔው ተገቢ አይደለም' ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ፡- "የማዕቀፍ እቅዱ መላክ አለመላኩን የበላይ አመራሩ ላያውቀው ይችላል። ቢያውቀውም ደግሞ ባለመገዛቱ የሚጎዳው መስሪያ ቤቱ ነው። እሱ ወይ ሊለቅ ይችላል በሌላ መንገድ እዛ ቦታ ባይኖር የሚጎዳው መስሪያ ቤቱ ስለሆነ አሰራራችሁ ተጠያቂነት እንዲኖርበትና አስገዳጅ እንዲሆን ያላቀረቡት ዩኒቨርሲቲዎች ያላቀረቡት መስሪያ ቤቶች ተጨማሪ ዕድል ይሰጣቸው"  ብለዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ በበኩላቸው የግዥ ፍላጎት  ያላቀረቡ ዩኒቨርስቲዎችና የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ዝርዝር መገለጽ ነበረበት ምክንያቱም መዘናጋት ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡ የአገልግሎቱ የስራ ሃላፊዎች የዕቃ ግዥ ፍላጎቱን ማሳወቅ ያልቻለ ተቋም በውሳኔው መሰረት ሊስተናገድ እንደማይገባ የወሰነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ተናግረዋል። ይህን ውሳኔ ያሳለፈው የምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተቋማት ፍላጎታቸውን ሳያሳውቁ በምን አይነት አግባብ ግዥ እንደሚፈጽሙ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግም አንስተዋል። አገልግሎቱ ከ2008-2010 በጀት ዓመት ከ49 አቅራቢዎች ጋር በመዋዋል ለመንግስት ባለ በጀት ተቋማት የማዕቀፍ ስምምነት ግዥ አገልግሎት ሲፈጽም ቆይቷል።   ይሁንና በ2010 በጀት ዓመት መንግስት ካደረገው የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ አቅራቢዎች የሚፈለገውን ዕቃ ለተቋማት ማቅረብ እንዳልቻሉ በውይይቱ ተነስቷል።   አገለግሎቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ማለትም ከ2011-2013 በጀት ዓመት ለሚከናወነው ግዥ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የዋጋ ማስተካከያ በማድረግ ግዥው እንዳይስተጓጎል ጥረት ይደረጋል ብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም