መንግስት ግጭትን አስቀድሞ የመከላከል እስትራቴጂ መቀየስ አለበት ተባለ

62
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 የኢትዮጵያ መንግስት አስቀድሞ ግጭትን የመከላከል እስትራቴጂ እንዲከተል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መከረ። ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን በመጪው ሳምንት የሚከበረውን 70ኛውን የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በዚሁ ወቅት ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት መንግስት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩትን ግጭቶች ለመከላከል እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ውጤት እያመጡ አይደለም። በመሆኑም ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር ይቻል ዘንድ  "ከእሳት ማጥፋት ዘዴ ወጥተን ዘላቂ የግጭት አፈታት፤ በተለይም አስቀድሞ ግጭትን የመከላከል እስትራቴጂ መከተል ይገባል" ብለዋል። ከምክር በዘለለ ዘላቂ የግጭት አፈታት ምን ሊሆን ይገባል በሚል ኮሚሽኑ ጥናት ማዘጋጀቱን ገልጸው በቀጣይም በጉዳዩ ላይ በህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እንደሚደረግ ገልፀዋል። "በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትን ለማክበርና ለማስከበር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ኮሚሽኑ በአወንታዊ መልኩ ያያል" ሲሉም ተናግረዋል። አክለውም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የሌሎች ጥረት ከታከለበት ብዙ አወንታዊ ለውጦች እንደሚመጡ በመግለጽ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ አስገንዘበዋል። የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሞሽነር በኢትዮጵያ ተወካይ ንዋንአኮላም ቭዊዲ በበኩላቸው ቀኑ የሚከበረው  በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር እየተወሰዱ ያሉ በጎ ተግባራትን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ገልፀዋል። የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን በ1950 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በየአመቱ የሰብአዊ መብት ቀን ሆኖ በየአመቱ ይከበራል። የፊታችን ሰኞ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በሚከበረው የዘንደሮው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን የኢትዮጵያ የእስካሁኑ የሰብአዊ መብት አያያዝ ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አንጻር የሚፈተሽ ይሆናል። በመርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፤ የሃይማኖትና የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም