በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው የበጋው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ይቀጥላል

126
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው የበጋው ደረቃማ የአየር ሁኔታ በሚቀጥሉት ቀናትም እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው ትንበያ መሰረት በአንዳንድ ደጋማ ስፍራዎች የሌሊቱ እና የማለዳው ቅዝቃዜ ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል። በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ ዝናብ ሰጭ የሜቲዎሮሎጂ ክስተቶች በተለይም በጥቂት የደቡብ ህዝቦች፣ የደቡብ ኦሮሚያና የደቡብ ሶማሌ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል። በተቀሩት የአገሪቱ ቦታዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚጠናከር ይጠበቃል ሲል አስታውቋል። በመሆኑም በሚቀጥለው ቀናት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የቤንች ማጂ፣ የከፋ፣ የደቡብ ኦሮሚያ፣ የጉጂና የቦረና ዞኖች፤ በሶማሌ ክልል የሊበንና የአፍዴራ ጥቂት ስፍራዎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል። የተቀሩት የአገሪቱ ስፍራዎች በአብዛኛው ደረቅ ሆነው ይቆያሉ። በትንበያው መሰረት በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ በቀጣይነት እንደሚስተዋልና በአንዳንድ አካባቢዎችም የተጠናከረ ቅዝቃዜ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል ብሏል ኤጀንሲው። ይህ ሁኔታ በተለይ የመኸር ሰብል ስብሰባና ድህረ ስብሰባ ላይ ለሚገኙ አካባቢዎች የዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን አመቺ እንደሚሆንና አርሶ አደሮችም በማሳ ላይ የሚገኙ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እንዲሰበስቡ ኤጀንሲው መክሯል። በሌላ በኩል ከደረቃማው የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ሊጠናከር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ሁኔታ በተለይ በመስኖ የሚለሙ ሰብሎች፣ አትክልቶችና፣ የፍራፍሬ ተክሎችን ሊጎዳና በእንስሳት ጤና ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል። በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው ደረቅ፣ ፀሃያማና ነፋሻማ ሁኔታ የሚያመዝን ቢሆንም አልፎ አልፎ የተመቻቹ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአገሪቱ ደቡባዊ አጋማሽ፣ ደቡባዊ ምስራቅና በመካከለኛው የሚገኙ ተፋሰሶች ላይ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል የኤጀንሲው ትንበያ ጠቁሟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም