በመዲናዋ 20 የመኪና ማቆሚያዎች በመጪው ዓርብ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ

68
አዲስ አበባህዳር 25/2011 በመዲናዋ የተዘጋጁ 20 የመኪና ማቆሚያዎች /ፓርኪንግ/ በመጪው ዓርብ ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 'ለልማት' በሚል ታጥረው የቆዩ ቦታዎችን ወደ መሬት ባንክ በማስገባት ላይ ይገኛል። የአስተዳደሩ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲም አጋጣሚውን በመጠቀም ወደ መሬት ባንክ ከገቡት ቦታዎች መካከል ለመኪና ማቆሚያ ይሆናሉ ያላቸውን እንዲፈቀዱለት ጠይቋል። የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኤጀንሲው ከጠየቃቸው 56 ቦታዎች እስካሁን 20ዎቹን በመፍቀዱ ለመኪና ማቆሚያ /ፓርኪንግ/ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርጓል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅሬኛ ሂርጳ እንደገለጹት ለፓርኪንግ የተዘጋጁት ቦታዎች በአራዳ፣ ቦሌ፣ ካዛንቺስና ሲኤምሲ አካባቢዎች ይገኛሉ። እነዚህ የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች በየአካባቢዎቹ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል። ወጣቶቹ በመኪና ማቆሚያዎቹ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በትኬት በሚሰበስቡት ክፍያ ገቢ ያገኛሉ። የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ለመኪና ማቆሚያ የተለዩት ቦታዎች ወደ ስራ እንዲገቡና ተጨማሪ ቦታዎች ተለይተው ግንባታ እንዲጀመር አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በዚሁ መሰረት ኤጀንሲው የጠየቃቸውን ቦታዎች ለመኪና ማቆሚያ አገልግሎት ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ተጨማሪ ቦታዎችን የመለየት ስራም እንደሚከናወን አቶ ጅሬኛ አስረድተዋል። ከመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጋር በመነጋገር በቦታዎቹ ቋሚና ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፎቆች /ስማርት ፓርኮች/ ለመገንባት መታቀዱንም ጠቁመዋል። በመጪው ዓርብ አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩት የመኪና ማቆሚያዎች የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባሻገር ለወጣቶች ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪ ብዛት ማስተናገድና የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ የሚያስችል ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የማስፋፋት ስራ በመከወን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በክፍያ የሚሠሩ 120 የመንገድ ዳር መኪና ማቆሚያዎች በጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በተደራጁ ወጣቶች እንደሚተዳደሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም