ሃገራዊ ለውጡን ከአዲሱ አመራር ጋር በመሆን እንደሚያስቀጥሉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

51
ወልዲያ ህዳር 24/2011 የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከአዲሱ አመራር ጋር በመሆን እንደሚያስቀጥሉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ባለፈው ዓመት በከተማው በተከሰተ ግጭት ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን ለማስታወስ ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል። የሰልፉ አስተባባሪ ወጣት ኤፍሬም አሰፋ እንደገጸው ሰላማዊ ሰልፉ በ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በወልድያ ከተማና አካባቢው በነበረው ግጭት ህይወታቸው ያለፉ ዜጎችን ለማስታወስ ታስቦ የተካሄደ ነው፡፡ "የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ከአዲሱ አመራር ጋር በመሆን እናስቀጥላለን" ያለው የሰልፉ አስተባባሪ የተካሄደው ሰልፍ ወጣቱ ከፓርቲ ነፃ በሆነ ማህበር በመደራጀት መብቱን እንዲያስከብር ለመቀስቀስም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለዜጎች ህይወጥ መጥፋት ምክንያት የሆኑ አመራሮች  ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቅ መሆኑንም ወጣት ኤፍሬም አስታውቋል፡፡ መንግስት አመራሮችን ሲሾም ህዝቡ ተወያይቶበትና የሚቀርቡ እጩዎችን አመኖባቸው መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ ጭምር ታስቦ ሰልፉ መዘጋጀቱን ወጣት ኤፍሬም አመልክቷል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ለሰልፈኞች ባሰሙት ንግግር ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ህይወታቸው ያለፉ ዜጎችን ለማሰብ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍና ወጣቱ ለለውጥ የከፈለውን መስዋዕትነት አድንቀዋል፡፡ ለውጡን የሚቃወሙ አካላት በሃይማኖትና በብሔር ልዩነት እያሳበቡ የሚፈጽሙትን ሴራ ወጣቱ ቀድሞ በመገንዘብ አላማቸውን እንዲያከሽፍ አስተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡ አመራሩ ለውጡን ተከትሎ በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግልም የህዝቡ ድጋፍና ይሁንታ ወሳኝ በመሆኑ ህዝቡም በሰከነ መልኩ ለውጡን ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጌታቸው ሃይሌ በሰጡት አስተያየት ጥር 12/2010 ዓ.ም በተነሳ ግጭት ልጃቸው የሚካኤልን ታቦት ለማስገባት በወጣበት ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል። ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ እሸቱ ጀመረ በበኩላቸው ታቦት በማጀብ ላይ የነበረ የ14 ዓመት ታዳጊ ልጃቸው በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ማለፉን አስታውሰዋል፡፡ "ልጆቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ህዝቡ የሚፈልገው ለውጥ መጥቷል" ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ በመስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ ቀጣይ እንዲሆን ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጸዋል። በሰዎቹ ላይ ተኩሰው የሰው ህይወት እንዲጠፋ ያደረጉ የጸጥታ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡም የሰልፉ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። በሰልፉ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም