ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያስፈልጋታል

139
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። የመጀመሪያው የኢትዮጵያና ቻይና የኢንዱስትሪ ትብብር የንግድ ትርዒት ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በተወካያቸው በኩል እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚያስፈልጋት ወቅት ላይ በመሆኗ የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር ወቅታዊና አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2017 ከቻይና የ4 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር ምርት ወደ አገር ውስጥ ያስገባች ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የ288  ሚሊዮን ዶላር ምርት ልካለች። በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ያለውን ልዩነት ለማጥበብም ብዙ መሰራት እንደሚገባ ተወካዩ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ አማካሪ ሊ ዩ እንዳሉት የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በማድረግ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር የቻይና መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል። ''ቻይና ግብርና ላይ በተመሰረተው ኢኮኖሚዋ በዓለም በሁለተኛ ደረጃ ወደሚገኝ ኢኮኖሚ መሸጋገር ችላለች'' ብለዋል። ቻይና በአሁኑ ወቅት ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገት ያከናወነቻቸው ተግባራት እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ጥሩ ማሳያ በመሆኑም የአገሪቱ መንግስት በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም አብራርተዋል። የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ አዘዘው እንዳሉት የቻይና አፍሪካ የንግድ ትርዒት በአገራቱ መካከል በማምረቻው ዘርፍ ያላቸውን ትስስርና የንግድ ልውውጥ የሚያጠናክር ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው 602 የቻይና ፕሮጀክቶች ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኩባንያዎቹ ለ38 ሺህ ቋሚና ለ41 ሺህ 600 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል። የቻይና ልዑካን ቡድን መሪ ሚስተር ሂ ካይሎንግ በበኩላቸው በንግድ ትርዒቱ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኩባንያዎች  በቻይና በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን በኃይል ማመንጫ፣ በግንባታ፣ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና ውጤቶች፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠናና በሌሎች ዘርፎችም የተሰማሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። የንግድ ትርዒቱ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ትርዒቱ በቻይና የዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ማዕከልና በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ የተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም