13ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ምክንያት በማድረግ የጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ትርኢትና ባዛር በአዲስ አበባ ተከፈተ

84
አዲስ አበባ  ህዳር 24/2011 13ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ምክንያት በማድረግ የጥቅቃቅና አነስተኛ የንግድ ትርኢትና ባዛር በአዲስ አበባ ተከፈተ። በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተው የንግድ ትርኢቱ ዛሬን ጨምሮ እስከ ህዳር 30 ይቆያል ። በአገር አቀፍ ደረጃ 131 ተሳታፊዎችን የያዘው የንግድ ትርኢቱ የባህል አልባሳት፣የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች የመሳሰሉት ቀርበዋል። የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሀመድ ረሺድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዓሉን ምክያት በማድረግ የተዘጋጀው ባዛርና የንግድ ትርኢቱ በክልሎች መካከል ያለው ትስስር እንዲጎለብት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን ከሸማች ማህበረሰብ  ጋር በማገናኘት የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ''በዓሉን ምክንያት በማድረግ ኀብረተሰቡ በአገሩ ምርት ተጠቃሚ እንዲሆንና አምራቹም ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማቅረብ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲሰፍን ማስቻል ሌላው ዓላማ መሆኑም ተገልጿል። እንደ አቶ  መሀመድ ገለጻ የንግድ ትርኢቱ የአገሪቷ ብሄር ብሄረሰቦች፣ባህልና ልምድ እንዲለዋወጡ ከማድረግ ባሻገር እርስ በእርስ በመተባበር ልማቱን የሚያቀላጥፉበትናጠንካራ ግንኙነት የሚፈጥሩበትም ነው። የበዓሉ ተሳታፊ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች በበኩላቸው የዘርፉ ዋናው ማነቆ የገበያ ትስስር አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው መሰል ዝግጅቶች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩ ናቸው፤ መቀጠልም አለበቸው ብለዋል። ወይዘሮ ኤልሳቤት ገቢሳ ከአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጥቃቅንና አነስተኛ የባህል አልባሳትና መጫሚያዎችን ይዘው ቀርበዋል። በዝግጅቱ ላይ በተደጋጋሚ መሳተፋቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ኤልሳቤት ''የተለያዩ ክልሎችን በባህል እንዳውቅና ግንኙነት እንድፈጥር ረድቶኛል'' ነው ያሉት። ''በንግድ ሥራ በኩልም አዳዲስ የንግድ ዘርፎች ላይ መሰማራት የሚያስችል ተሞክሮ እየቀሰምን ነው'' ሲሉም ተደምጠዋል። እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ካልመጡ ሥራዎቻችን አይታወቁም፤አይታዩም የምትለው ደግሞ ከባህርዳር የቆዳ ውጤቶች ይዛ የቀረበችው ወጣት ሀረግ ዘነበ ናት። 13ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ''በብዘሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ አዘጋጅነት ህዳር 29 ይከበራል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም