ሰላም በህጻናት አንደበት

82
አዲስ አበባ  ህዳር 24/2011 ሰላም ከሌለ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም እንደፈለጉ በልተው ጠጥተው ማደርና መንቀሳቀስ እንደማይችሉ እሙን ነው። በሰላም እጦት ምክንያት ደግሞ ክፉና ደጉን የማይለዩ፣ ነገ አገር ተረካቢና የአገር አለኝታ የሆኑ ህጻናት፣ ሴቶች፣ የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ታትረው የሚሰሩ ወጣቶች እንዲሁም ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን ይበልጥ ተጎጂዎቹ ስለመሆናቸውም አያጠያይቅም። ለመሆኑ ስለ ሰላም ትርጉም ምን ያህሎቻችን እንረዳ ይሆን? ሰላም በህጻናት አንደበት "የዓለም መፈጠር ምክንያት"፣ የሰው ልጆችና በምድር ላይ የሚኖሩ ነገሮች ሁሉ "የመኖራቸው ምሳሌ" ነው ሲሉ ይገልጹታል። በተለይ ህጻናት ተምረው ራሳቸውን ለመለወጥና አድገው አገራቸውን ለመጥቀም እንዲችሉ የአንድ አገር ሰላም መረጋገጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የህጻናት ፓርላማ አባሎች ይናገራሉ። ለዚህም እንደ ጥጃ ቦርቀው፣ እንደ አውሮፕላን በረው ተምረውና መልካም ነገር አንግበው ወደፊት ለአገራቸው አለኝታ ለሚሆኑ ህጻናት ሰላምን መስከብ እንደሚገባም ይገልጻሉ። ከሶማሌ ክልል ህጻናት ፓርላማ የሆነው ህጻን ወባህ ጀማል እንዳለው "ሰላም ማለት ብርሃን ነው ሰላም ከሌለ ጨለማ ነው እኛ ያለነው አሁን በሰላም ነው ሰላም ከሌለ እንዲህ አብሮ መሆንና ማውራት አይቻልም፣ ሰው ወጥቶ አይገባም፣ ምግብ አይበላም፣ ውሃም አይጠጣም፣ ሰላም ከሌለ እድገት አይገኝም፣ እድገታችን ሁሉ መሬት ላይ ነው የሚሆነው።" "ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም ሰላም ካለ ግን ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት ከአካባቢ ማህበረሰብ፣ ከተለያዩ ክልሎች አንድ ላይ ተባብሮ በፍቅር መኖር ይቻላል፣ ሰላም ከሌለ ግን ብሄር ለብሄር ተለይቶ የነበረን አንድነትና በአንድ ተባብሮ የመኖር እሴታችን ይጠፋል፤ በመሆኑም ሰላም ለእኔ ሁሉም ነገር ነው ብዬ አስባለው" በማለት የሚናገረው ˝  ህጻን ሚሊያና አለን ከትግራይ ክልል ህጻናት ፓርላማ  ነው፡፡ ሰላም ተመራጭ መሆኑ መታመኑ ብቻውን ሰላምን ለማስገኘት አይበቃም፤ በኃላፊነትና በእኔነት ስሜት ተቀብሎ መተግበርንም ጭምር ይጠይቃል። በመሆኑም ስለ ሰላም ምንነትና አስፈላጊነት በመስበክ ረገድ ከቤተሰብ ጀምሮ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አካላትም ጭምር ተግተው መስራት ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም