በጭልጋ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

61
ጎንደር ህዳር 23/2011 በማዕካላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ  ዛሬ ጧት በደረሰ የተሽከከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በአምስት ሰዎች ላይ  ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ። የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ተወካይ ኃላፊ ዋና ሳጅን ሞላ ዘነበ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው 15 ሰዎችን ጭኖ ከመተማ ወደ ጎንደር ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ከጎንደር ወደ ሱዳን 400 ኩንታል ባቄላ ጭኖ ከሚጓዝ ከባድ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ነው። የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-15551 አ.ማ የሆነው ሚኒባስ ሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -87598 ኢት ከሆነ ባለ ተሳቢ የጭነት መኪና ጋር የተጋጨው ዛሬ ጧቱ 2:00 ሰዓት ላይ በወረዳው ዋሊደባ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሲሆን በአደጋው የሚኒባሱን አሽከርካሪ ጨምሮ የአራት ሰዎች ህይወት ወድያውን አልፏል፡፡ በሌሎች አምስት ተሳፋሪዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የገለጹት ዋና ሳጅን ሞላ በአደጋው ይህወታቸው ያልፈ ሰዎችን አስከሬን ተጣርቶ ወደየቤተሰቦቻቸው መላኩን ገልፀዋል። ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአይከል ሆስፒታል የህክምና ድጋፍ ተደርጎላቸው ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጎንደር ቲቺንግ ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውን ገልጸው ለጊዜው የተሰወሩትን የጭነት መኪናውን አሽከርካሪና ረዳት ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። አሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰናቸውን በመጠበቅ የሰዎችን ህይወትና ንበረት ከአደጋ ለመከላከል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኢኒስፔክተር ሞላ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም