በትግራይ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭት መጠን መጨመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ

65
ማይጨው ህዳር 23/2011 በትግራይ ክልል የኤች .አይ. ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭት መጠን መጨመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ አለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ትላንት በመኾኒ ከተማ ተካሂዷል ። በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች.አይ. ቪ .ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጣዕመ ዘገየ በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት ባለፈው አመት 1 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው በዚህ አመት በ0 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል። በህዝቡና በአመራር አካላት የተፈጠረ መዘናጋት፣ የህዝባዊ ማህበራት ተሳትፎ መላላት፣  የቤተሰብ ጥምር ጤና ፓኬጅ አገልግሎትና  የኤች. አይ.ቪ. ኤድስ ክበባት እንቅሰቃሴ መዳከም ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የደም መመርመሪያ ቁሳቁሶች እጥረት፣ የበሽታው ተጋላጮችን ያማከለ  የምርመራ አገልግሎት ያለማካሄድና ሌሎችንም በተጨማሪ ምክንያትነት አንስተዋል። ከህገ-ወጥ ፅንስ ማቋረጥ ጋር ተያይዞ የሴቶች የበሽታው ተጋላጭነት ከወንዶች በእጥፍ ማደጉንም  አስተባባሪው  ገልጸዋል። በተለይም በክልሉ ደቡባዊ ዞን አላማጣና ማይጨው ከተሞችና ራያ ዓዘቦ ወረዳ የቫይረሱ ስርጭት በስፋት የሚያይባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። "የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረግ ጥረት ለአንድ አካል የሚተው ሳይሆን የሁሉንም የተቀናጀ ተናትፎ የሚጠይቅ ነው " ያሉት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተክላይ ወልደማርያም ናቸው "የፖለቲካ አመራርና የኤች. አይ.ቪ. ኤድስ መከላከያ ምክር ቤት ቦርድን የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ለማሻሻል የተቀየሰው አቅጣጫ ተግባራዊ ይደረጋል" ብለዋል፡፡ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ የሲቪልና የህዝባዊ ማህበራት፣ የህዝብ አደረጃጀቶችና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ማህበራትን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል ። "ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ  በሆኑ አካባቢዎች የቀን ሰራተኞች፣ ተንቀሳቃሽ ነጋዴዎች፣ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎችና ወጣቶች ላይ ያተኮረ የደም ምርመራ አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ ይካሄዳል " ብለዋል ። የክልሉ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ገብረመድህን ሐጎስ የቫይረሱ ዋንኛ ተጠቂ ወጣቱ ክፍል መሆኑን ተናግሯል ። "በክልሉ ባለፉት አራት ወራት ምርመራ ካደረጉ 25 ሺህ ወጣቶች ውስጥ 1ሺህ 444ቱ ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቷል" ሲል ለአብነት ጠቅሷል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ማህበሩ ከ11 ሚሊዮን በላይ ኮንዶሞችን ማሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡ "የክልሉ የኤች. አይ.ቪ. ኤድስ ፖዘቲቭ ጥምረት የቫይረሱን ስርጭ ለመግታት  የድርሻውን እየተወጣ ነው " ያሉት ደግሞ  የጥምረቱ ሊቀመንበር አቶ መድሃኒየ ገብረመድህን ናቸው፡፡ ጥመረቱ በ37 ማህበራት የተደራጁ ከ17 ሺህ በላይ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ሊቀ መንበሩ ገለጻ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ አባላትም ከልቅ ግብረ -ስጋ ግኑኝነት በመታቀብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ በክልሉ ከ600 በላይ በጎ ፈቃደኞችን ያሳተፈ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች እንክበካቤና ድጋፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም