ለትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኬት የትምህርትና ስልጠና ሴክተሩ የሚያፈራቸው ዜጎች ብቃት ወሳኝ ነው – ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም

904

ሃዋሳ ህዳር 22/2011 ለሃገሪቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስኬት የትምህርትና ስልጠና ሴክተሩ የሚያፈራቸው ዜጎች ብቃት ወሳኝ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም አስታወቀ፡፡

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአምስተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 76 የህምክና ዶክተሮች ዛሬ አስመርቋል፡፡

በምረቃው ላይ የተገኙት ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበለጸጉና ባልበለጸጉ ሃገራት መካከል የሚታየው የቴክኖሎጂና የሃብት ልዩነት ለትምህርትና ስልጠና በሰጡት ትኩረት የተወሰነ ነው ብለዋል፡፡

በሃገሪቱ ያሉ ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በአቅርቦት ተገቢነትና በጥራት የስራው አለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከማፍራት አንጻር ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች ይቀሯቸዋልም ነው ያሉት፡፡

ለሃገሪቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስኬት የትምህርትና ስልጠና ሴክተሩ የሚያፈራቸው ዜጎች ብቃት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ መመደቡንም ተናግረዋል፡፡

የተቋማቱ ምሩቃን የሃገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ከመለወጥና  የህዝቡን አኗኗር እንዲሻሻል ከማድረግ አንጻር ብዙ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ለዚህም የከፍተኛ ትምህርትን ተገቢነትና ጥራት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህምክና ሙያ ከተጎዳና ከተጎሰቆለ በህይወት ለመኖር ከሚመኝ ታማሚ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ በባለሙያው ላይ ያረፈው ሃላፊነት እጅግ ከፍተኛ ነው ያሉት፡፡

በታዳጊ ሀገር እንዳለ ዜጋ ችግሮችንና መሰናክሎች በተገቢው መንገድ በመጋፈጥ ሃለፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ደርዛ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ህክምና ትምህርት ቤት የዛሬዎቹን ጨምሮ በአምስት ዙር 317 ሃኪሞች ማስመረቁን ተናግረዋል፡፡

በሌሎች የጤና ዘርፎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎች ማፍራቱን ገልጸው በየአመቱ የሴት ህክምና ዶክተር ተመራቂዎች ቁጥር መጨመሩንና ከዘንድሮ ተመራቂዎቹ 18ቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ በሚቀጥሉት ዓመታት በስሩ ያሉ የቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በማሳደግ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ላይ የምርምርና የህክምና ማእከል በመክፈት እያስገነባ ባለው ሪፈራል ሆስፒታል ችግር ፈቺ ምርምሮችን እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡

መንግስት ለህብረተሰቡ ጤና መሻሻል እያደረገ ያለውን ርብርብ ለማገዝ የዘርፉ ምሩቃን ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በሙሉ አቅም በማገልገል ለሃገሪቱ ህዳሴ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትለወጥ ከሆነ የወጣቶች በተለይም የወጣት ሃኪሞች ተሳትፎና አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆን አለበት ያለችው ደግሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ተወካይ ዶክተር መስከረም አለቃ ናት፡፡

በማህበራትና ክበባት ከመሳተፍ ባለፈ ወጣቱ በጤና ፖሊሲው፣ በአካባቢው በሃገረ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጪ ሚና እንዲጫወት ተባብሮ ተደራጅቶ መስራት ይገባል ብላለች፡፡

በትምህርት ክፍሉ 3.54 በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ዶክተር መሰረት ሙሉ ተመራቂዎች ቃል የገባነውን በመፈጸም ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብሏል፡፡

አንገቱ ላይ ያጠለቀውን  ሜዳሊያ በሰው ህይወት የመሰለው ተመራቂው ሃላፊነቴን ሳልወጣ ስቀር  የሰውን ህይወት አደጋ ውስጥ እንደምጥል አስቤ የማህጸንና ጽንስ ሃኪም ለመሆን ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡

በዝግጅቱ የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳዳሪን ጨምሮ የተመራቂ ቤተሰቦችና የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡