ኢህአፓ በሃገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ አስተሳሰብ መጎልበት እሰራለሁ አለ

87
ደሴ ህዳር 22/2011 በዶክተር ዐቢይና ባልደረቦቻቸው የተጀመረው አዲስ የለውጥ አስተሳሰብ እንዲጎለብት የድርሻውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) አስታወቀ። ፓርቲው በደሴ ከተማ ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ጀሚል መሐመድ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የተጀመረውን የለውጥ አስተሳሰብ በማጎልበት በሃገሪቱ የሚስተዋሉ ስጋቶች እንዲቃለሉ ሰላማዊ ትግሉን አጠንክሮ ይቀጥላል። ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡና ሃገራዊ አንድነት እውን እንዲሆን ከ40 ዓመታት በላይ ፓርቲው መታገሉን ገልጸው በቀደመውና በአሁኑ ወጣት ትውልድ መካከል ያለውን የጋራ ዓላማ በማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል። ፓርቲው በረጅም የትግል ተሞክሮው ውስጥ ያጋጠሙት ስህተቶች እንዳይደገሙ፣ የትግል ጽናቱና መልካም ተግባራቶቹ እንዲቀጥሉ ለአዲሱ ትውልድ ዓላማውን የማስተዋወቅ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ጀሚል ጠቁመዋል፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም በበኩላቸው ፓርቲው ህብረ-ብሔራዊ ፕሮግራም ካላቸው ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከሚያራምዱና ለዴሞክራሲ ስርዓት እውን መሆን ከሚታገሉ ድርጅቶች ጋር ተዋህዶ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከውይይቱ ተሳታፊ አባላት መካከል አቶ ፍስሃ ቦጋለ ኢህአፓ ወጣቱ ትውልድ ዓርማውን አንስቶ እንዲከተለው ኢትዮጵያዊነትን ከሚያቀነቅኑ፣ ተመሳሳይ የፖለቲካ አቅጣጫ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ውህደት በመፍጠር ራሱን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ቀደም ሲል ተመሳሳይ ውይይቶችን በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች ማካሄዱ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም