የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ምክር ቤት በድህነት ተኮር መስሪያ ቤቶች የተከናወኑ ተግባራትን ገመገመ

739

ሰቆጣ ህዳር 22/2011 የዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 5ኛ አመት 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤው በድህነት ተኮር መስሪያ ቤቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተወያየ ነው፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ሃይሉ ሚሰው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ዛሬ በተጀመረው የምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባኤ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የቀረበውን ያለፉት ሦስት ዓመታት የድህነት ተኮር ተቋማት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።

የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና አርሶ አደሩ በምግብ ራሱን እንዲችል በሚደረገው ጥረት ተቋማቱ  በግብዓት አቅርቦት ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከመሙላት አንጻር በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ በጉባኤው ተመላክቷል፡፡

አርሶ አደሩ በአካባቢው ያሉትን ወንዞች በዘመናዊ መንገድ ማልማት የሚያስችሉት የመስኖ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በምክር ቤቱ አቅጣጫ መቀመጡን አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡

እየተገነቡ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችም ቢሆኑ የሚስተዋልባቸውን የጥራት ችግር በመቅረፍ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲከናወኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅን መሰረት በማድረግ ህብረተሰቡ በአሳ ሃብት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሟላ የክልሉ መንግስት  ትኩረት እንዲያደርግበት  በምክር ቤቱ ተገምግሟል፡፡

በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ሊቀረፉ እንደሚገባም የምክር ቤት አባላቱ ገምግመው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎች የማቋረጥ እና የመድገም ምጣኔ አሃዝን ዝቅ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የትምህርት ተቋማትና መምህራን እንዲሁም ወላጆች በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባ በምክር ቤቱ ተመላክቷል፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሳተላይትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 874 የዳስና የዛፍ ጥላ መማሪያ ክፍሎችን የክልሉ መንግስት  ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ወደ ግንባታ መቀየር እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ፕላዝማ እና ኮፒውተር ተሟልቶላቸው በመብራት አቅርቦት ችግር ምክንያት ለተማሪዎች አገልግሎት ያልሰጡ ትምህርት ቤቶች አማራጮችን በመጠቀም ወደ ስራ ሊገቡ እንደሚገባ ምክር ቤቱ ገምግሟል፡፡

በሰቆጣ፣ ጽፅቃና መሸሃ ከተሞች ላይ የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በክልሉ መንግስት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ በተኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክር ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ መምከሩን አቶ ሃይሉ ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ጉባኤውን በነገ ውሎው በቀጣይ የሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በተሳካ ሁኔታ የሚከናወኑበትን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው በተጓደሉ የመምሪያ የስራ አስፈጻሚዎች ምትክ የአዲስ አመራሮችን ሹመት መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡