የግጭቶች መንስኤ ትውልድ የመቅረፅ ባህል ደካማ መሆን ነው - አስተያየት ሰጪዎች

133
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 በአገሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤው ትውልድ የመቅረፅ ባህሉ ደካማ መሆን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ መምህራን ገለጹ። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት፣ ለመፈናቀል፣ ለችግርና እንግልት ዳርገዋል። ግጭቶች ብሔር ተኮር ሲሆኑ መዳረሻቸውን በማስፋት በነገ አገር ተረካቢዎች ላይ እያሳደሩት ያለው ተፅእኖ ትውልዱን በመቅረፅ ረገድ ያለውን ደካማ ባህል የሚያሳዩ እንደሆኑ መምህራኑ ይናገራሉ። ትውልድን በመልካም ምግባር በመቅረፅ ረገድ ለሚስተዋለው ክፍተት ወላጆች፣ መምህራንና መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ እንዳለባቸውም ይስማማሉ። መምህር ፈቃዱ በላይ ህጻናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስለ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት፣ ስለ መካባበርና መቻቻል በአግባቡ እንዲረዱ ቢደረግ "የአሁኖቹ ግጭቶች ባልኖሩ" ይላሉ። በተለይም "እኛ መምህራን ትውልድ የመቅረጽ ሃላፊነታችንን ለመወጣት ያደረግነው ጥረት በቂ ያለመሆንና መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ማነስ ዋጋ አስከፍሏል" ብለዋል። በቀጣይ ያለፈውና የሚመጣውን ትውልድ የመቻቻልና የመከባባር ባህል ለማጎልበት "ያለሰለሰ ጥረት ይጠይቃል እኔም ለዚህ ዝግጁ ነኝ" ሲሉ አክለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ መምህር ሳሙኤል መርዴ እንደሚሉት ደግሞ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶች መነሻ የራስ ወዳድነት መንፈስ የተጠናወታቸው ዜጎች መበራከት ነው። የአገሪቱን ህዝቦች የጋራ እሴቶች በማስፋት በኢትዮጵያዊነታቸውና በባህላቸው የሚኮሩ ዜጎችን የማፍራት ስራ መጠናከር አለበት ይላሉ። እንደ መምህሩ ገለጻ በትምህር ቤቶች የስነ ዜጋ ትምህርትን በአግባቡ ያለማስጨበጥና ወጥነት ባለው መንገድ ያለመስጠት ችግርም አለ።    ችግሩን ለመፍታት መምህራን፣ ወላጆችና መንግስት በጋራ በተጀመረው አዲስ የለውጥ ጎዳና አዲስ አሰራር መፍጠር አለባቸው ብለዋል። ተማሪ ጁሊያና ደሳለኝና ተማሪ አቅሌሲያ ፈቃደስላሴ በበኩላቸው በሚሰጣቸው ትምህርት ኢትዮጵያን የመቻቻልና የመከባባር ባህል ያላት ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም