በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚስተዋለው የተዛባ አመለካከት እየተሻሻለ መጥቷል

58
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚስተዋለው የተዛባ አመለካከት እየተሻሻለ መጥቷል ሲሉ የአካል ጉዳተኞች ገለፁ። ቆየት ባሉ ዓለም አቀፍ አሃዛዊ መረጃዎች መሰረት በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ የተለያየ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ትምህርትንና የስራ እድልን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የፖሊሲና ሌሎች ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ይገልፃል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ከተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት እንዲቀየርም የግንዛቤ ማስፋፊያ መርሃ ግብሮችም ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆናቸውም ይነገራል። በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ በስራም ሆነ በሌሎች መስኮች ለአካል ጉዳተኞች ያለው የተዛባ አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ሲሉ ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች በሰጡት አስተያየት የተናገሩት። በበተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታየው ድጋፍ እያደገ መምጣቱንም አካል ጉዳተኞቹ ገልፀዋል። በአዲስ አበባ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጣሪ ሰራተኛ የሆነው ጥላሁን ጀማነህ በሰጠው አስተያየት ከዚህ በፊት በስራም ሆነ ሌሎች ማህበረሳባዊ ጉዳዮች ላይ አካል ጉዳተኞችን የማሳተፍ ልምዱ ደካማ እንደነበር ጠቅሶ ይህ የተዛባ አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን  ነው የገለጸው። አክሎም "አሁን ላይ በብዙ ሰው ዘንድ አካል ጉዳተኞች እንደማኛውም ዜጋ መስራት ይችላሉ የሚለውን አመለካከት ጥሩ በሚባል ደረጃ እየተሻሻለ መጥቷል፤" ብሏል። ይሁን እንጂ አሁንም ራሳቸው አካል ጉዳተኞች ጠንከራ ሰራተኛ በመሆን አቅማቸውን  ማሳየትና እንደ ግለስብም ሆነ እንደ አገር አውንታዊ አመለካከት በማጠናከር መንግስትን ጨምሮ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስቧል። በግል ሥራ የሚተዳደሩተ ሌላዋ አካል ጉዳተኛ ወይዘሮ አሹ አየነው በበኩላቸው በህብረተሰቡ ዘንድ "አካል ጉዳተኛ ምንም ነገር ማድረግም ሆነ መፍጠር አይችሉምም የሚለው የማህበረሰቡ የተሳሳተ አመለካከት እየቀነሰ መሆኑ ይሰማኛል" ብለዋል። ይሁን እንጂ አሁንም እኩል እንደሌሎች ዜጎች የማየትና በምጣኔ ኃብታዊ እና ሌሎች ዘርፎች ጋር በተያያዘ ተጠቃሚነታቸውና ተሳታፊነታቸው እንዳያድግ የሚያደርጉ ማነቆዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት። በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ስጦታው ሁነኛው በበኩላቸው መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም በትምህርትና ሌሎች ዘርፎች እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ፣ ምቹ የሥራ ቦታንና ትራንስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎችን በማመቻቸት ረገድ ያለው ትኩረት ሊጠናከረ ይገባዋል ብለዋል። ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ከነገ በስቲያ ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። ቀኑ በኢትዮጵያም በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ይውላል። መንግስት በዓሉን በማስመልከት በሰጠው መግለጫ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች ለመፍታት የአካል ጉደተኞች ማህበራት፣ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተሰማሩ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የሚዲያ አካላትና ሁሉም ህብረተሰብ በተቀናጀ መልኩ መስራት  እንደሚጠበቅባቸው  አሳስቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም