የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በመላ አገሪቱ የሚያደርጉትን የሠላም ጉዞ ጀመሩ

104
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በሁሉም ክልሎች የሚያደርጉትን የሠላም ጉዞ ዛሬ ጀመሩ። "ስለ አገራችን ሠላም ዝም አንልም" ያሉት የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎቹ ጉዞ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ያለመ  መሆኑን የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታውቋል። የሰላም ጉዞው “ሰላም ለሁላችን በሁላችን“ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማጠናከርና እያንዣንባበ ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚያስችል ውይይት የሚካሄድበት ነው። የጉባኤውን የበላይ ጠባቂዎች፣ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት፣ የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ሕብረት አባላት፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተው የሰላም ጉዞ ውይይት በትግራይ ክልል የሚጀመር መሆኑ ተገልጿል። በየክልሎቹ የሚካሄዱት ውይይቶች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የክልል አስተዳደሮችና ከፍተኛ አመራሮችን ያሳትፋሉ። ውይይቱ ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማረጋጋጥ የሚያስችል መግባባትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተነግሯል። በአገሪቱ ከነባሩ የኢትዮጵያዊያን ባህልና ሀይማኖታዊ እሴት በሚቃረን መልኩ በህዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚያደርጉ የጥላቻ ንግግሮች፣ ጽንፍ የወጣ የዘረኝነትና የብሄርተኝነት ቅስቀሳዎች እየተበራከቱ መሆኑን የጉባኤው መግለጫ ጠቅሷል። በግጭቶች ሳቢያ በርካቶች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን፣ ህይወት ማለፉን ፣ የአካልና ሌሎች ጉዳቶች መከሰታቸውንና በቅርቡም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶች መነሳታቸውን አውስቷል። ግጭትን መከላከል የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አገራዊ ሀላፊነት በመሆኑ አባቶች ነጻና ገለልተኛ በመሆን አባታዊ ምክርና ተግሳጽ በመስጠት የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቋል። አገሪቱ ተደማጭነት ያላቸውና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ረገድ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ያሏት መሆኗም በመግለጫው ተመልክቷል። በመሆኑም አባቶች ወደ ሁሉም ክልሎች በመጓዝ ከህዝቡ ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱባቸውን አቅጣጫዎች ለማመላከት መዘጋጀታቸውን ነው ጉባኤው ያስታወቀው። በህግና በአሰራር የሚፈቱ ችግሮች ላይ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅና ከአገሪቷ መልካም እሴቶችና የሁለም ሀይማኖቶች አስተምህሮት የሆኑት ይቅርታና ዕርቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር እንደሚደረግም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም