በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የወላጆችና የትምህርት ተቋማት ሚና መጎልበት አለበት

57
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 የአገርን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆምና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የወላጆችና የትምህርት ተቋማት ሚና መጎልበት እንዳለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አሳሰቡ። 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል አስመልክቶ ከ10 ሺህ በላይ ወጣት ተማሪዎች የተሳተፉበት የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ተካሂዷል። የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ወጣቶች የብሄር ብሄረሰቦችን የመከባበርና የመቻቻል ባህል የማዳበር ኃላፊነታቸውን እንዲያጎለብቱ ከትምህርት ተቋማት ጀምሮ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። ትውልዱ በስነ-ምግባር ታንጾ እንዲያድግ የስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ትምህርትን በማጠናከር ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያለው እንዲሆን የማድረግ ስራም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት። ወጣቶች በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ በአስተሳሰብ ቀረጻ ላይ በሚሰራው ስራ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ቢኖርበትም የወላጆችና የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል። በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የእርስ በእርስ ግጭት ዘርን መሰረት ያደረገ ጥላቻና ለሕብረ-ብሔራዊነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመመከት ረገድ ወጣቶችና ተማሪዎች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸውም ብለዋል። በተለይ ወጣቶች አንድ የሚያደርጓቸውን በማጉላት ልዩነታቸው ውበት መሆኑን በማመን ዘርን መሰረት ያደረገ ጥላቻን ለማጥፋት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በትምህር ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የወጣቶችን እርስ በእርስ የመደማመጥና የመከባበር ባህል ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ነው ወይዘሮ ኬሪያ የተናገሩት። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው በዓሉ በአብሮነት የመኖር ባህልን በማጠናከር ጠንካራ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚከበር ገልጸዋል። የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ሆና መከበሩ ልዩ የሚያደርገው ሲሆን ወጣቱ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመመከት ያለውን አቋም የሚያጠናክርበት እንደሚሆን አክለዋል። 13ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም