በጎ ፍቃደኞችን የሚያስተባብር ተቋማዊ አሰራር ሊኖር ይገባል

70
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጎ ፍቃደኞችን የሚያስተባብር ተቋማዊ አሰራር ሊኖር ይገባል ተባለ። የዓለም አቀፍ በጎ ፍቃደኛ ቀን የማነቃቂያ ፅሁፎች በቀረቡበት የፓናል ውይይት ተከብሯል። በማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲና የበጎ ፍቃደኞች አስተባባሪ መላኩ ኃይሉ የተዘጋጀው የዘንድሮው በዓል "በጎ ፍቃደኞች ጠንካራ ማህበረሰቦችን ይገነባሉ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው። በአገሪቱ በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም በበጎ ፍቃድ ስራ የሚሳተፈው ጥቂት መሆኑን የገለጸው መላኩ ኃይሉ በተለይም ወጣቱ በዚህ ተግባር እንዲሳተፍ ስራውን የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት ሊኖር እንደሚገባ አመልክቷል። የተቋማዊ አሰራር መኖር ህጻናት ከትምህርት ቤት ጀምሮ በበጎ ፍቃደኝነት ማገልገልን እንዲለምዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስችላል። በተጨማሪም በበጎ ፍቃደኝነት ማገልገል የሚሹ ሰዎች መረጃ አግኝተው ማገልገል የሚፈልጉበትን ዘርፍ እንዲመርጡም እድል ይፈጥራል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ተቋማዊ አሰራሩ በበጎ ፍቃድ ተግባር ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖርና መተባበር እንዲጎለብት ይረዳል። የበዓሉ ተሳታፊ በጎ ፍቃደኞችም አገርን ለመለወጥ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት። ተማሪ ብሌን ፀጋዬ ከልጅነቷ ጀምሮ ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት እንደነበራት አስታውሳ የዛሬ ሶስት ዓመት ክብረ አረጋዊያን ምግባረ ሰናይ ድርጅት ገብታ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት መጀመሯን ገልጣለች። "የመረዳዳት ባህል ቢኖረንም በተለይ ደራሽ አደጋ ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ በጎ አድራጎት የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል" ብላለች። "ዛፍ ፍሬውን ለሰው ዝናብም እርጥበቱን ለመሬት እንደሚለግሱ ሁሉ ሰውም ያለውን ለሌለው መስጠት ይገባዋል" ያለው ደግሞ መሀመድ ኢብራሂም ነው። የበጎ አድራጎት ተግባራት መበራከትና እርስ በርስ መረዳዳት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገውን ጉዞ እንደሚደግፍ ገልጿል። የበጎ ፍቃደኛ ቀን በየዓመቱ ህዳር 26 ቀን የሚከበር ሲሆን ዓላማውም ለበጎ ፍቃደኞች እውቅና መስጠት፣ በጎ ፍቃደኛነትን ማስተዋወቅና መንግስታት በጎ ፍቃደኞችን እንዲደግፉ ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም