አገር ዓቀፉን የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር በወንዶች አማራ በሴቶች አዲስ አበባ አሸነፉ

73
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 በአገር ዓቀፉ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር በወንዶች አማራ ክልል በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ የዋንጫ አሸናፊ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ላለፉት ስድስት ቀናት ያካሄደው ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል። በውጤቱም በወንዶች አማራ ክልል በአንደኝነት በማጠናቀቅ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። በዚህ ውድድር አዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ሁለተኛና ሶስተኛ በመውጣት በቅደም ተከተላቸው የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ሴቶች የዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሸናፊ በመሆን ዋንጫና ተጫዋቾቹም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በወንዶች ውድድር አንደኛ የሆነው አማራ ክልል በሴቶችም ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ መውሰድ ችሏል። ኦሮሚያ ክልል ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ክልሎች እንደ ደረጃቸው የሶስት፣ ሁለትና አንድ የዊልቸር ሳይክል ሽልማት አበርክቷል። ውድድሩ የተዘጋጀው ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ነው። በኢትዮጵያ ይህ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ሲዘጋጅ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም