በቫይረሱ ይብለጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩር አድርጌ እየሰራሁ ነው - ጽህፈት ቤቱ

139
ሰመራ/ አሶሳ ህዳር 22/2011 በአፋር ክልል የኤች ኤይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ለበሽታው ይብለጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩር አድርጎ እየሰራ መሆኑን የአፋር ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልም የኤች አይ ቪ ኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራን ሊያጠናከሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ የአፋር ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሎ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት 10 አመታት የክልሉ መንግስት የኤች አይ ቪ ኤድስን ስርጭት ለመከላክል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሰርቷል፡፡ በተሰራው ስራ የበሽታውን ስርጭት ከሶስት ነጥብ ሰባት በመቶ ወደ ዜሮ ነጥብ 92 በመቶ እንዲቀንስ ማድረግ ተችሎ አንደነበር የተናገሩት ኃላፊው እ.ኤ.አ በ2016 የኢትዮጵያ ሰነተዋልዶ ጤና ይፋ ያደረገው ጥናት በክልሉ የቫይረሱ ሰርጭት ከዜሮ ነጥብ 92 ወደ አንድ ነጥብ አራት  ከፍ ማለቱን አስታውቋል፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋት በመፍጠሩ የበሽታው ስርጭት መልሶ እንዲያገረሽ ማድረጉን አቶ አሎ ሁሴን ገልጸዋል፡፡ የመሰረተ-ልማት መስፋፋትን ተከትሎ ፈጣን በሆነው የከተሞች እድገት ምክንያት ከገጠር  ቀበሌዎች ጋር መቀራረብ መፈጠሩ ለቫይረሱ መስፋፋት የራሱ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመካከልም በተያዘው በጀት አመት ከክልሉ የሃይማኖት አባቶች፣ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጃት አንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ  የማህበረሰብ ውይይትና የህዝብ የንቅናቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የኤች አይቪ ኤድስ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ከፍሎችን ማዕከል ያደረገ  ነጻ-ምርመራ፤ የምክርና ህክምና አገልግሎቶችን እየተሰጡ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ የአፋር ክልል ኤች ኤቪ ኤድስ በደማቸዉ የሚገኝ ማህበራት ህብረት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ኡስማን ሃሰን ማህበሩ በክልሉ በ20 ወረዳዎች ከሁለት ሺህ 500  በላይ አባላትን አቅፈው  የሚገኙ 20 ማህበራት መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ ማህበሩ ከቫይረሱ ጋር  አብረው የሚኖሩ በጎ ፈቃደኞችን በመጠቀም ተመርምረው ራሳቸውን ላወቁ አዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች የህይወት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ የኢትዩ-ጂቡቲ አስፓልት ዳር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞችና በሜጋ ፕሮጀክቶች አካባቢ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በወር አንድ ጊዜ የአቻ ለአቻ ትምህርት በመስጠት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በሎግያ ከተማ የወገን ለወገን ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ማህብር አባል የሆነችው አሰለፍ ይማም  ከቫይረሱ ጋር መኖር ከጀመረች ከ12 አመት በላይ እንደሆናት ተናግራለች፡፡ ከመንግሰት በምታገኘው ድጋፍና በማህበሯ ጽህፈት ቤት ውስጥ ባገኘችው ስራ በመታገዝ ህይወቷን እየመራች እንደምትገኝ ገልጻለች፡፡ ዘንድሮ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ከ128 ሺህ 557 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ ምርመራና የምክር አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን ከአፋር ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ኤድስ ቀን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ደረጃ ትናንት በአሶሳ ከተማ ተከብዋሯል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ግሩም ባዩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የኤድስ በሽታ ስርጭት አንድ በመቶ ይጠጋል፡፡ “በክልሉ በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል በሽታውን በመከላከል ረገድ ቅንጅታዊ አሰራር የለም” ያሉት አቶ ግሩም በየደረጃው የሚገኙ የኤች.አይቪ ኤድስ ምክር ቤቶች እንቅስቃሴ እንደተዳከመ መምጣቱን  አስረድተዋል፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ማህበራት እንቅስቃሴም የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ስራ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳያመጣ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራን ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃብታሙ ታዬ በበኩላቸው የክልሉ ነዋሪዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤችአይቪ/ኤድስ ምርመራ በማድረግ የጤንነታቸውን ሁኔታ ማወቅ ቀዳሚ ተግባር እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም ወጣቱን ከአደንዛዥ ዕጽ መከላከልና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጸታዊ ጥቃት ማስቆም በሽታውን በመከላከል ረገድ ድርሻው ከፍተኛ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለዚሁ ተግባራዊነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም