በአማራ ክልል ኤች አይቪ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንዳልሆነ ተገለፀ

112
ባህር ዳር ህዳር 22/2011 በአማራ ክልል ኤች አይቪ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ  የበሽታው ስርጭት ዳግም እንዲያገረሽ አድርጎታል ሲሉ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች ተናገሩ። በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የወጋገን በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማንአስብ መኮነን ለኢዜአ እንደገለጹት በሽታውን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር በመቀዛቀዙ በተለይ በወጣቱ ላይ መዘናጋት እየተፈጠረ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተደራጀ መንገድ የቅስቀሳና የማስተማር ስራ ይከናወን እንደነበርና በዚህም ወቅት ህብረተሰቡ ስለበሽታው አስከፊነት እንዲያውቅና ራሱን እንዲጠብቅ አድርጎት መቆየቱን ተናግረዋል። ''በተለይም ከሁለት ዓመት ወዲህ ረጅ ድርጅቶች በመውጣታቸው ይሰጥ የነበረው ትምህርት እየተቀዛቀዘ መጥቷል'' ብለዋል። በዚህም በባህርዳር ከተማ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት እየጨመረ እንዲመጣና አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ወደማህበሩ እየተቀላቀሉ እንደሆነም አስረድተዋል። የተስፋ ጎህ ባህርዳር ቅርንጫፍ የአባላት ተጠሪ ወይዘሮ አለሚቱ ወርቁ በበኩላቸው ቀደም ሲል በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በዕምነትና በትምህርት ተቋማት፣ በመናኽሪያና በገበያ ቦታዎች ሳይቀር የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፍሉ ነበር። አሁን ላይ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይሰራ የነበረው የመከላከል ስራ ትኩራት በማጣቱ ህብረተሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይም በሁለተኛ ደረጃ፣ በዩኒቨርሲቲና ሌሎች ቦታዎች በመገኘት በአፍላ ዕድሜ ለሚገኙ ወጣቶች ስለበሽታው ስርጭትና አስከፊነት ትኩረት ሰጥቶ ግንዛቤ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ኤች አይቪ በጎ አድራጎት ማህበራት ህብረት ዳይሬክተር አቶ መሸሻ መርዕድ በበኩላቸው ስለኤች አይቪ የተሰጠው ትኩረት እየተቀዛቀዘ መምጣት በክልሉ የበሽታው ስርጭት ከሀገር አቀፉ በላይ ሆኖ እንደተገኘ በጥናት ተረጋግጧል። ቀደም ሲል ኤች አይ ቪ የሚያደርሰውን ጉዳት በተደራጀ አግባብ የቅስቀሳና የማስተማር ስራ በመከናወኑ የበሽታው ስርጭት ቀንሶ እነደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ የማስተማር ስራው በመቆሙ በሽታው መልሶ ሊያገረሽ ችሏል። በክልሉ ከ54 ሺህ በላይ አባላትን የያዙ 163 ማህበራት ቢኖሩም የግሎባል ፈንድ ተጠቃሚ ከሆኑ 44 ወረዳዎች በስተቀር ሌሎች ማህበራት እየተደገፉ ባለመሆኑ የመከላከል ስራ እየተሰራ አይደለም። በመሆኑም ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የኤች አይቪ ኤድስን ጉዳይ ሁሉም ህብረተሰብ የእኔ ነው ብሎ በመከላከልና በመቆጣጠር ትውልዱን ማዳን ይገባል ሲሉ ገልፀዋል። በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቀጣጠር ዘርፈብዙ ምላሽ ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ውድነህ ገረመው በበኩላቸው በክልሉ የበሽታው የስርጭት መጠን አንድ ነጥብ ሁለት በመቶ ላይ ይገኛል። የስርጭቱ መጠን ከሀገር አቀፉ በተለየ መንገድ የአማራ ክልል የመጨመር ሁኔታ እንዳለው ገልጸው፤ ስርጭቱ የታየባቸውን አካባቢዎች በመለየት የመከላከሉ ስራ እየተሰራ ነው። ስርጭቱ ከጨመረባቸው የክልሉ ከተሞች ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻ፣ መተማ፣ ደሴና ደብረ ማርቆስ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ሲሆኑ በማደግ ላይ የሚገኙ የገጠር ከተሞችም የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የችግሩ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ የቀን ሰራተኞች ላይ ያተኮረ ግንዛቤ በመፍጠር የበሽታውን ስርጭት የመከላከልና መቆጣጠር ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። በክልሉ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተካሄደ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ምርመራ 446 ሺህ ሰዎች የተመረመሩ ሲሆን አራት ሺህ 400 የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ ተረጋግጧል ብለዋል። በክልሉም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ከ137 ሺህ በላይ ወገኖች የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት እየወሰዱ እንደሚገኙም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም