የጥራት ጉድለት በተገኘባቸው 665 የምግብና መጠጥ ተቋማት ላይ እስከ እገዳ የሚደርስ እርምጃ ተወሰደ

114
አዲስ አበባ ህዳር 21/2011 በአዲስ አበባ የጥራት ጉድለት በተገኘባቸው 665 የምግብና መጠጥ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማው ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ ባለስልጣን አስታወቀ። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት በአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ ላይ የተወሰደው እርምጃ ለጤና አደገኛ መሆናቸው የተረጋገጡ  ምግቦችንና መድሃኒቶችን ማስወገድንና የሥራ እግድን የሚያካትት ነው ተብሏል። አገልግሎታቸው የጥራት ጉድለትና ለጤና አደገኛ መሆኑ የተደረሰበት ባለስልጣኑ ምርመራና ክትትል ካደረገባቸው 8 ሺህ የሚልቁ የምግብና መጠጥ ድርጀቶችና ኢንዱስትሪ ተቋማት መካከል ነው። ባለስልጣኑ የህዝብ ጤንነትን ከአደጋ መከላከል እንዲቻል የምግብ፣ መጠጥና መድኃኒት አቅርቦት ጤንነቱ፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን የቁጥጥርና ክትትል ሥራ የሚያከናውን መንግስታዊ አካል ነው። ለህዝብ ጤና አደገኛ በሆነ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የንግድ ፍቃድ መንጠቅን ጨምሮ በህግ አስከመጠየቅ የሚደርስ እርምጃ ይቀጥላል ተብሏል። ዋና ዳሬክተሩ አቶ ጌታቸው ወረቲ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መስሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት ባካሄደው ፍተሻ መሰረት እርምጃ የተወሰደባቸው ከፍተኛ ችግር የታየባቸው ናቸው። ባለስልጣኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ምግቦችም እንዲወገዱ ማድረጉን አቶ ጌታቸው ይገልፃሉ። በተጨማሪም በለስላሳና የአልኮል መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተደረገ የቁጥጥርና ፍተሻ 4ሺ 612 ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች ተወግደዋል። በጤናና ጤና ነክ የሆኑ ተቋማት ላይ በተደረገ የቁጥጥር ደግሞ በመደኃለኒትና የህክምና መሳሪያዎች  ጽዳት አጠባበቅ ላይ መጠነኛ ክፍተት በመታየቱ  ከማስጠንቂቂያ እስከ እገዳ የዘለቀ እርምጃ መውስዱን ዋና ዳይሬክተሩ አክለግ ተናግረዋል። ይህ የቁጥጥርና የፍተሻ ስራ በሩብ  ዓመቱ ብቻ የተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳሬክተሩ በባለስልጣኑ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የአሰራር ሂደቶችን ጠብቀው የሚሄዱ በመሆኑ በቀጣይ ከንግድ ፍቃድ መቀማት እስከ ፍርድ ቤት ክስ የሚያመራ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ አያይዘውም በ2011 ሩብ ዓመት በምግብ እና መጠጥ ተቋማት ፍቃድ እድሳትን በተመለከተ ለ1 ሺህ 295 ያህል ተቋማት  የንግድ ፍቃደ እድሳት ማድረግ መቻሉንም እንዲሁ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም