የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለፀ

70
ደሴ ህዳር 21/2011 የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጡ እየተሻሻለ መምጣቱን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡ ሆስፒታሉ በበኩሉ የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አቶ ከድር አሊ ከዚህ ቀደም ባለቤታቸውን ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ይዘው ቢመጡም የኤክስሬይ መሳሪያ አይሰራም በሚል አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልቻሉ አስታውሰዋል፡፡ የሆስፒታሉ ኤክስሬይ መሳሪያ አገልግሎት ከሚሰጥበት የማይሰጥበት ይበልጥ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጭው አገልግሎቱን ለማግኘት እስከ 400 ብር ለግል ጤና ተቋማት መክፈላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሆስፒታሉ የአሰራር ግድፈቱን አስተካክሎ የአሰራር መሻሻል ማሳየቱንና በዚህም የቅርብ ቤተሰባቸው ኤክስሬይ ታዞለት አገልግሎቱን በፍጥነት ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ወይዘሮ ዘሪቱ አህመድ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ካለው ደረጃና የተጠቃሚ ህዝብ ቁጥር ብዛት አንጻር የሚጠበቅበትን እየሰራ ነው ማለት ባይቻልም ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ መጠነኛ መሻሻል እንዳሳየ አብራርተዋል፡፡ በተለይ የህክምና ዶክተሮች ከዚህ ቀደም ከሆስፒታሉ ስራ ይልቅ ለግል ስራቸው ቅድሚያ ስለሚሰጡ ፈጣን አገልግሎት በማጣት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ተፈላጊውን ሃኪም በአጭር ጊዜ ውስጥ አግኝተው ልጃቸውን ማሳከማቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ አሁንም ከሆስፒታሉ ደረጃ አንጻር ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ስላልተሟሉለት አሁንም ህሙማን ለግል ጤና ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል በመታከም ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የካርድ ክፍልና የመረጃ አያያዝ ስርአቱ አሁንም እንዳልተሻሻለ የገለፁት ደግሞ በደሴ ከተማ መናፈሻ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ወይንሸት ጫኔ ናቸው፡፡ የተጠናከረ የህሙማን የምርመራ ማህደር አያያዝ ስለሌለ በየወቅቱ ከመዝገብ ቤት መረጃ ለማውጣት ከሶስት ሰዓት ያላነሰ ሰልፍ እንደሚሰለፉ ገልጸዋል፡፡ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ የሱፍ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ከባለ ድርሻ አካላት፣ ከህዝቡና ከባለሙያዎች ጋር ያደረገው ሰፊ የግምገማ መድረክ ለአገልግሎቱ መሻሻል አስተዋጽኦ እንዳደረገለት አስታውቀዋል፡፡ እንደ ስራ አስኪያጁ ህዝብን ማእከል ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት ባደረገው ጥረትም ባለፈው አንድ ወር ውስጥ 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መድኃኒት በማስመጣት የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ተደርጓል፡፡ የላብራቶሪ ክፍሉንም ለማጠናከር 3 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ዓይነቱን ከ53 ወደ 70 ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊ የሲቲ ስካን ማሽን በ6 ሚሊዮን ብር ተገዝቶ ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱን ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ በአሁኑ ሰዓት ማሽኑ የሚቀመጥበት ክፍል እየተገነባ እንደሆነና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት ሊጀምር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች የህክምና ግብአቶችም ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡ በካርድ ክፍልና በመረጃ አያያዝ የሚስተዋለውንም ችግር ለመቅረፍና አገልግሎቱን በኮምፒወተር የተደገፈ ለማድረግ አሜሪካን አገር ከሚገኘው ቱሊን ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት መፈጸሙን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ200 በላይ ኮምፒውተሮችን ለሆስፒታሉ ማበርከቱን ከአቶ ሰይድ ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል በየዓመት ከሰሜን ምስራቅ አማራና ከአፋር ክልል የሚመጡ ከ8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም