ከ20 ዓመት በኋላ በአክሱም ህዳር ጽዮን በዓል መሳተፋችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል - ኤርትራዊያን

73
አክሱም ህዳር 21/2011 በኢትዮ - ኤርትራ በተፈጠረው የሰላም ስምምነት ከ20 ዓመት በኋላ በአክሱም ህዳር ጽዮን በዓል በመሳተፋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ኤርትራውያን ምእመናን ገለጹ፡፡ ኤርትራውያኑ ለኢዜአ እንደገለጹት በተደረገላቸው ወንድማዊ አቀባበልና በዓሉ ላይ በተሰማው  ሰላም፣ ፍቅና አንድነትን የሚሰብክ ዝማሬ ልዩ ሀሴት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡ ከአስመራ ከተማ የመጡ አቶ ዳዊት ኪዳነ በሰጡት አስተያየት እንደገለፁት ከረጅም አመታት በኋላ የአክሱም ህዳር ጽዮን በዓልን ለማክበር አክሱም ከተማ ሲደርሱ በተደረገላቸው አቀባበል እና በዓሉን ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በማክበራችው የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል ህብረተሰቡ በየእምነቱ ስለ ሰላም መስበክ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ''በደምና በሃይማኖት የተሳሰርን በመሆኑ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል'' ብለዋል። አቶ ወልደጋብር ይሳቅ በበኩላቸው ከአቀባበሉ ጀምሮ እስከ በአሉ አከባበር የነበረው የህዝብ ፍቅርና አንድነት የሚያስደስት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኤርትራውያን ከ20 አመት በኋላ በእንደዚህ አይነቱ በአል መሳተፋቸው ልዩ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡ ''በአክሱም ማርያም ጽዮን መገኘታችን አስደስቶናል ሰላም ስለተፈጠረ ነው እዚህ የተገኘው፣ የተገኘውን ሰላም ለማጠናከር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በአሉ ትልቅ ፋይዳ አለው'' ብለዋል። ''በታላቁ በዓል ከወንድሞቻችን ጋር አብረን በፍቅርና በአንድነት ማክበራችን ዳግም የተወለድን አድርገን ነው የምናስበው''  ያሉት ደግሞ ሌላኛው ከአስመራ ከተማ የመጡ አቶ ሃፍቶም ተፈሪ ናቸው። ''ከአሁን በኋላ ማንም አይለየንም፤ አንድ ህዝብ ነን ፍቅርና አንድነት ለትውልዱ ማስተላለፍ አለብን'' ብለዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ በመጨረሻም በሁለቱ ሀገራት መካከል እርቀ ሰላም እንዲመጣ ጥረት ላደረጉ የሀገራቱ መሪዎች አመስግነዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም