መረጃ ሰጪ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆነ

2102

አዲስ አበባ ህዳር 21/2011 የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ለአንድ ማዕከል ተገልጋዮች ቅድመ-መረጃ የሚሰጥ የሞባይል መተግበርያ ስራ ላይ አዋለ።

ላለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ መገናኛና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ ሲለማ የቆየው የሞባይል መተግበሪያ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀንበር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የሞባይል መተግበሪያው በአንድ ማዕከል የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ያደርገዋል።

ህብረተሰቡ ለአገልግሎት ወደ ቢሮ ከመሄዳቸው በፊት ማሟላት የሚገባውቸውን መረጃ ስለሚሰጥ የማይገባ ምልልስና እንግልትን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

በተጨማሪ ስለሚሰጡ አገልግሎቶች ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

የሞባይል መተግበሪያውን ያስተዋወቁት የአዲስ አበባ መገናኛና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ ኃላፊ ዶክተር አቢዮት ባዩ መተግበሪያው ከቀድሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደተሰራ ገልፀዋል።

መረጃው በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዝርዝር፣ አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስፈልጉ ነገሮችና ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ያለውን የተቋማት አድራሻ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ስራ የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን በቀጣይ ወደ ተግባር የሚገባው ሁለተኛው ዙር መተግበሪያ ደግሞ ተገልጋዮች ካሉበት ሆነው የኦንላይን ምዝገባና አገልግሎት የሚያገኙበት እንደሚሆን አስታውቀዋል።

ተገልጋዮች አንድ ጊዜ ብቻ ኢንተርኔትን በመጠቀም ጉግል ፕሌይ ላይ በእንግሊዝኛ AAMSEDB ወይም ADDIS ABABA MICRO AND SMALL ENTERPRISE DEVELOPMENT BUREAU የሚለው ፅፈው አፕሊኬሽኑን በማውረድ መጠቀም እንደሚችሉ አስታውቀዋል።