ተማሪዎች ችግሮችን በውይይት በመፍታት ግጭትን ሊከላከሉ ይገባል-ሴት የሰላም አምባሳደሮች

623

ሰመራ ህዳር 21/2011 ተማሪዎች ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታት ግጭትን ሊከላከሉ እንደሚገባ ሴት የሰላም አምባሳሮች መከሩ።

ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ሴት የሰላም አምባሳደሮች  በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ትናንት መክረዋል፡፡

ከትግራይ ክልል የተወከሉት ወይዘሮ ጃኖ ንጉሰ ተማሪዎች ከአላስፈላጊ ግጭቶች በመቆጠብ ችግሮቻቸውን በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ መክረዋል ።

“ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በማስፈን አላማችሁን ልታሳኩ ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል ።

ግጭትና ጥላቻን ለሚያናፍሱ አልባሌ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች ቦታ መስጠት እንደሌለባቸውም አሳስበዋል ።

ከኦሮሚያ የተወከሉት ወይዘሮ አልፊያ ሃጂ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ተጎጂዎች ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸው ጭምር ሰለባዎች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ችግሩ የመተሳሰብ ባህላዊ እሴታችን በሂደት እየተሸረሸሩና እየተበረዙ በመምጣታቸው ጭምር የተፈጠረ በመሆኑ ተማሪዎች ግጭትን በመከላከል ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ሊያሰፍኑ እንደሚገባ መክረዋል ።

የሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎችም ተማሪዎችን በመምከርና በመገሰፅ ጭምር  ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ከሌሎች አካባቢዎች ወደ አፋር ዩኒቨርሲቲ ለመጡ ተማሪዎች ህብረተሰቡ የእናታዊና አባታዊ ፍቅር በመስጠት እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የገለፁት ደግሞ የአፋር ክልልን የወከሉት ወይዘሮ መዲና ማሐሙድ ናቸው።

የዩኒቨርስቲው ተማሪ ትግስት ገብሬ ሴት የሰላም አምባሰደሮች እናቷን እንዳስታወሷት በመግለፅ ተቸግረው ያስተማሯት እኗቷን ውለታ ለመመለስ በትምህርቷ ውጤታማ ለመሆን እንደምትተጋ ገልጻለች ።

ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻዋን እንደምትወጣ አረጋግጣለች ።

ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ በክልሉ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል ።