የደቡብ ኮሪያ ባቡር ለመጀመረያ ጊዜ የሰሜን ኮሪያን ድንበር ተሻግሮ ጉዞ ጀመረ

1103
ህዳር 21/2011 የደቡብ ኮሪያ ባቡር ከረጂም ዓመታት በኋላ  ለመጀመረያ ጊዜ የሰሜን ኮሪያን ድንበር ተሻግሮ ጉዞ ጀመረ።
ባቡሩ ከ10 ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን ድንበር አልፎ የሰሜን ኮሪያ ወሰን የተሻገረው።
በውስጡም የሰሜን ኮሪያን የባቡር መስመር ለማዘመን ጥናት የሚያካሂዱ የደቡብ ኮሪያ ባለሙያዎችን አሳፍሯል።
ሁለቱ ኮሪያዎች ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት እያሻሻሉ አሁን ከፍ ወዳለ ደረጃ አድርሰውታል።
ሁለቱ ሀገራት በትራንስፖርትና በንግድ የመተሳሰር ተስፋቸው መለምለሙንም መረጃዎች ያሳያሉ።
ባሳለፍነው ሚዘያዚያ ወር የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በተገናኙበት ታሪካዊ አጋጣሚ የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን የሀገራቸው የባቡር መስመሮችን ማሻሻል እንደሚፈልጉ የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን መጠየቃቸው ይታወሳል።
የተወሰነው መሰረተ ልማት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የተሰራ በመሆኑ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለመገናኘት ሙሉ ለሙሉ መሻሻል አለበት የሚል እሳቤ ላይ መደረሱም ተገልጿል።
ዛሬ የተላኩትን 28 የደቡብ ኮሪያ ባለሙያዎች ከፓንሙን ጣቢያ ጀምሮ የሰሜን ኮሪያ ባቡር አሳፍሯቸው እንደሚጓዝ ተገልጿል።
ባለሙያዎቹ ለሚቀጥሉት 18 ቀናት 1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የባቡር መስመር መሰተ ልማት እንደሚያጠኑ ተጠቁሟል።