የህግ የበላይነትና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አንድምታ

117
በዳግም መርሻ /ኢዜአ/ በጥር ወር 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው ሰላሳኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው ሙስናን ነበር። በአውሮፓውያኑ 2018 ዓ.ም «The African Anti-Corruption Year» (የሙስና መዋጊያ አመት) በማለትም ሰይመውታል። ይህ የሚያሳየው ሙስና በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ዴሞክራሲን፣ የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግርን፣ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ምን ያህል አሳሳቢና ወቅታዊ አደጋን እንደጋረጠ ነው። ስያሜውም ከዚህ መንፈስ የመነጨ  መሆኑን መገመት ይቻላል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አፍሪካ በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር በሙስና ታጣለች፡፡ይህ ማለት የአህጉሪቱ 25 በመቶ ጥቅል ምርት ማለት ነው፤ ወይም የአንድ ዓመት የኢትዮጵያ በጀት፤ በሌላ አገላለጽ 148 ቢሊዮን ዶላር እየተሰረቀ ያለው የመቶ ሚሊዮንን ሕዝብ የእለት ጉርስ በንፈግ ነው፡፡ ስርቆቱ እየተፈፀመ ያለው ደግሞ በአመዛኙ  በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በሸሪኮቻቸውና በዘመድ አዝማዶቻቸው፣ በትላልቅ ኩባንያዎች፣ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት… ወዘተ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ሙስና ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል። በተለይ ከአስር አመታት ወዲህ ሙስና በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ሄዶ አጠቃላይ የስርአቱ መገለጫ በሚያስብል ደረጃ አደጋ እስከመሆን ደርሷል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም ባወጣው የሀገራት የሙስና ደረጃ መዘርዝር መሰረት ኢትዮጵያ ከመቶ ሰማንያ ሀገራት መቶ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዚሁ በተለያየ ዘርፍ የሚታዩ የአስተዳደር ብልሽቶችን በሚጠቁመው መስፈርት ከመቶ ያላት ሰላሳ አምስት ነጥብ ብቻ ነው። በሌላ በኩል Global Financial Integrity የተባለው አለም አቀፍ ተቋም ከአለም ባንክና ከአለም የገንዘብ ድርጅት ያገኘውን መረጃ በመመርኮዝ ባወጣው ሪፖርት እ.አ.አ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኢትዮጵያ ወደ 12 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጪ ተሸጋግሯል። የአፍሪካ ህብረት «ሀይ ሌቭል ፓናል» በ2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት የሚያሳየው በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍና በሀይድሮ ኤሌክትሪክ ዘርፍ ያለው ሙስና ለህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ነው። በኢትዮጵያ የሚታየው ሙስና፣ የተደራጀ ዝርፊያና ብልሹ አሰራር አዲስ ነገርአይደለም፤ የቆየና በጊዜ ሂደት ስር እየሰደደ የመጣ ችግር ነው እንጂ። «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» የሚለው በሹመት ጊዜ ጥቅምን ማካበትን እንደ ጥሩ ነገር የሚሰብከው የቆየው ብሂላችን አብዛኛው ህብረተሰብ ለሙስና ያለውን አስተሳሰብና አተያይ ያንጸባርቃል። ከተወሰኑ አመታት ወዲህ ግን በሀገሪቱ ያለው ሙስናና ሌብነት በቢሮክራሲው ውስጥ ዘወትር ከሚታየው የተለመደ አነስተኛ ሙስናና ብልሹ አሰራር አስደንጋጭና አሳፋሪ ወደሆነው ግዙፍ የምዝበራ አይነት (Grand Corruption) መሸጋገሩ ያደባባይ ሚስጢር  ነው። አሁን አሁን  በኢትዮጵያ ከምንም ተነስተው ብዙ የማይሰሙ ሚሊየነሮች ተፈጥረዋል። ህገወጥ በሆነ መንገድ ባካበቱት ሀብት ህዝብ የሚጠቋቆምባቸው ህንጻና ፎቅ ከተማ ውስጥ ገንብተው አከራይተዋል። በጥቂት ጊዜ ውስጥም ወደ ትልቅ ኢንቨስተርነት ተለውጠዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒትስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት የነገሱ መሆናቸውን ደጋግመው ስናገሩ እናስታውሳለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ላነሱት ሀሳብ ብዙ ነገሮችን በማስረጃነት ያቀርቡ ነበር፤ ያለግባብ እየከበሩ ያሉ ሰዎች የሰበሰቡትን የሀብት ብዛትና  ምንጭ  ለመሸፈን ሲሉ በተለያዩ ስሞች፤ ለአቅመ-አዳም ባልደረሱ ልጆቻቸው ጭምር እንደሚያስመዘግቡት፤ አንዳንዶች በውሾቻቸው ስም ሳይቀር የንግድ ፈቃድ እንደሚያወጡ፤ ከዚያም አልፎ በሳቸው ግምት በቤት ኪራይ መልክ አገሪቱን ለቆ የወጣው ሀብት በአሜሪካ ዶላር እስከ ሁለት ቢሊዮን እንደሚደርስ ተናግረው ነበር። በሌላ ጊዜም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከተናገሯቸው መካከል የመንግሥትን ግብር መንግስት ብቻ የሚሰበስብ አለመሆኑንና ከመንግሥት ውጪ የመንግሥትን ግብር እየሰበሰቡ ያሉ ሁለት ክፍሎች እንዳሉ ነው የጠቀሱት። አንደኛው የመንግሥት ሌባ፤ ሁለተኛው ደግሞ የግል ሌባ ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር። እነዚህ ሁለቱ አንድ ላይ ሆነው ለመንግሥት መግባት የሚገባውን ይካፈሉታል ማለታቸውንም  እናስታውሳለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ«መንግስት በአንድ እጅ ነው ሙስናን የሚታገለው» ብለውም በወቅቱ ተናግረው ነበር። አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝም ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ስለሙስና ጎጂነትና አደገኛነት ደጋግመው ይናገራሉ፤  በአንድ ወቅት ለፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ ፀረ ሙስናን ራሳቸው ትኩረት አድርገው እንደሚከታተሉ ለሕዝብ ቃል ገብተው ነበር፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ያካሄደውን የጥናት ሪፖርት ይፋ ሲያደርግም እንዲሁ ስለሙስና አምርረው ተናግረው ነበር፡፡ መሪዎቹ ስለ ሙስና ጎጂነት ደጋግመው በአደባባይ አስተያየት የመስጠታቸውን ያህል በሙስና ላይ ተጨባጭና ህዝቡን የሚያረካ ውጤት አስመዝገበዋል? የጸረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልስ በቂ አመራር ሰጥተዋል? የሚሉት ጉዳዮችም ብዙ አሉታዊ ትችቶችን ሲያስነሱ ቆይቷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለብልሹ አሰራሮችና ለሙስና ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ወይም እጃቸው አለበት ተብለው የሚጠረጠሩ አመራሮችና ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር ማዋልና ለህግ ተጠያቂ በማድረግ የተጠናከረ እርምጃ ሲወሰድ አልተስተዋለም። ይልቁንም የሙስናና የብልሹ አሰራር ችግሮችን ለመፍታት መንግስት አብዛኛው ትኩረቱ በከፍተኛ እርከን ላይ ከሚገኙት ዋነኛ ተጠያቂዎች ሳይሆን ትናንሽ አሳዎች ወይም  መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች ላይ ትኩረቱን ያደርግ ነበር። በዚህ ምክንያትም በሙስና ላይ የሚደረገው ትግል የሚያመረቃ ውጤት አላመጣም። ህዝቡም በመንግስትና በጸረ ሙስና ትግሉ አመኔታው እየተሟጠጠ ሄዶ ነበር። ለዚህም መንግስት በተደጋጋሚ ይሰጠው የነበረው ምክንያት መረጃና ማስረጃ ለማግኘት የተቸገረ መሆኑን  ሲሆን ይህ በብዙዎች ዘንድ ውሀ የማያነሳ ምክንያት ነበር። ችግሩን ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመፍታት በቂ አቅምና መረጃ ያለው መንግስትና ተቋማቱ እንጂ ህብረተሰቡ አይደለምና። ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ተብሎ በመንግስት የተቋቋሙ እንደ ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን፣ የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት፣ የአቃቤ ህግ፣ እንባ ጠባቂ ተቋምና ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የመሳሰሉ ተቋማት  ቁርጠኛ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ያህል ተንቀሳቅሰው ትርጉም ያለው ስራ እንዳልሰሩ ይተቻሉ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙስናን በተመለከተ በፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በየመንፈቁ የሚቀርብለትን ሪፖርት ከማዳመጥ ባለፈ በራሱ ተነሳሽነትና ባሉት ቋሚ ኮሚቴዎች ምርመራና የማጣራት ስራ ሰርቶ ችግር ያለባቸውን አካላት(ተቋማት) መስመር በማስያዝ  ጠንካራ ሚና አልነበረውም። የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽንም መዋቅሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመና በፊት  የነበሩት እንቅስቃሴዎችም እየቀነሱ የመጡበት ሁኔታ እንዳለ መታዘብ ይቻላል። ቀደም ሲል ኮሚሽኑ የነበረው የሙስና ወንጀልን መርምሮ ለህግ የማቅረብ ስልጣን ለፌዴራል ፖሊስና ለአቃቤ ህግ በመሰጠቱ የቀድሞ የነበረውን ቁመናና ጥንካሬ ይዞ ሊቀጥል አልቻለም። ይህ ታዲያ በጸረ ሙስና ትግሉና እንስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን መታዘብ ይቻላል። መንግስት ሁሌም “ሙስናን እየተዋጋሁ ነው… የስርአቱም አደጋ ነው” እያለ ሲናገር የቆየ ቢሆንም ሲወሰዱ የነበሩት እርምጃዎች ግን ከነበረው አሳሳቢ ሁኔታና ከችግሩ ስፋት ጋር የሚመጣጠን አልነበረም። ለሙስና ትግል የመንግስት ቁርጠኝነት ማጣት የሀገር ኢኮኖሚ እንዲታመም ከማድረጉ ባሻገር የህዝብ ጥያቄና አመጽ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስፋት እንዲነሳና እንዲቀጣጠል በማድረግ፤ ብዙ ጉዳት እንዲደርስ ገፊ ምክንያት ሆኖ በመጨረሻም አሁን ለምንገኝበት ሁኔታ እንድንደርስ አድርጎናል። ከሰባት ወር ወዲህ በኢትዮጵያ በፖለቲካውና በማህበራዊ መስኮች ከዚህ በፊት ሊሆኑ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይችሉ አዳዲስ ለውጦች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት እየተመዘገቡ ሲሆን እነዚህ የለውጥ ብልጭታዎች ነገ ወገግ ያለ ብርሀን እንደሚመጣ ህዝቡ ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቅባቸው አድርገዋል። ተስፋን ከሚያጭሩ ጉዳዮች አንዱ ከሰሞኑ  ስልጣንና የሀላፊነት ቦታ ተገን በማድረግ ሀገር ያላትን ሀብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ መዝብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት መሆናቸውና እርምጃውም ተጠናክሮ መቀጠሉ ነው። በአቃቤ ህግ በእማኝነት የተዘረዘሩት አስደንጋጭ የሙስናና የሌብነት ድርጊቶች አዲስ ነገር ሳይሆኑ ህዝብ ለረጅም አመታት እርስ በርሱ ሲነጋገርባቸው የነበሩ፤ ተጨባጭ  እርምጃ ባለመወሰዱ ያሁኑ አደገኛ ሁኔታ ላይ የደረሱ ናቸው። ለአብዛኛው ህብረተሰብ አዲስ የሆነውና ለማመን የሚከብደው በአቃቤ ህግ የተዘረዘሩት የሙስና ወንጀሎችና ምዝበራዎች ያን ያህል ስፋት ይኖራቸዋል ተብሎ ያለመገመቱ ነው ብዬ አስባለሁ። ሌላው ህዝቡ ብዙም  ያልጠበቀው ነገር መንግስት ሙስናና ሌብነትን ለመዋጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑ ነው። የተጀመረው የጸረ-ሙስና ዘመቻና እርምጃው እንደ ሀገር ምን ትርጉም አለው? ምንስ አንደምታ ይኖረው ይሆን? ብሎ ሀሳብ ማንሳት ጠቃሚ ነው። እንደ እኔ እምነት መንግስት ይፋ ያደረገልን መጠነ ሰፊ ምዝበራና የሙስና ተግባር ብዙ ትርጉምና አንደምታ አለው። በአቃቤ ህግ እንደተነገረን ከሆነ ሜቴክ ለተለያዩ ትላልቅና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማስኬጃ በማለት በየጊዜው የወሰደው ነገር ግን የት እንደገባ የማይታወቅና የተመዘበረ የሀገሪቱ ሀብት በቢሊዮን ይቆጠራል። የገንዘብ ምንጩም በአብዛኛው በብድር እንደሆነ ይነገራል። ታዲያ በብድርም ይሁን በህዝብ መወጮ ለልማት ተብሎ የተሰበሰበው  የሀገር ሀብት ለታሰበለት አላማ ቢውል ባለከፋ ነበር። የሚቆጨው በዚህ መልኩ የተገኘን ገንዘበ ለታሰበለት አላማ በትክክል ከማዋል ይልቅ ለዘረፋና ለብክነት መዳረጉና ይሰራሉ የተባሉት ፕሮጀክቶችም መና ሆነው የሀብረተሰቡን ችግር መፍታት ያለመቻላቸው ነው። ሀገሪቱ ያለብዙ ተጨማሪ እሴት ከፍተኛ የብድር ወለድ ከፋይ መሆኗና  ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ መግባቱ ሲታሰብ እንደ ሀገር አሳዛኝ፣ አሳፋሪም፣ አስደንጋጭም ነው። ይህ ሁሉ ችግር ለምን ተከሰተ? እንደዚህ አይነት ሀኔታ ውስጥ  እንዴት ልንገባ ቻልን? የሚሉ ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢና ለወደፊት አካሄዳችንም የሚጠቅም ይመስለኛል። በአኔ ግምት አሁን ሚስጢሩ አደባባይ ለወጣው ከፍተኛ ምዝበራና ብልሹ አሰራር በር የከፈተው ለትላልቅና በተለይም በሀገራችን በአይነታቸው አዳዲስ ለሆኑ ፕሮጀክቶች እውቀት፣ ችሎታና የስራ አመራር ክህሎት የሌላቸው አካላት ያለ ሙያቸውና ከቆሙበት አላማ ውጭ በድፍረት ትልቅ ሀላፊነት እንዲሸከሙ መደረጉ ነው።  ለዚህም እንደማሳያ የሚጠቀሰው ሜቴክ  ባለው የአቅምና የብቃት ማነስ ምክንያት ሳያጠናቅቃቸው በእንጥልጥል የቀሩት ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት ሜቴክን እንኳን የህዳሴ ግድብን የመሰለ ትልቅ ፕሮጀክት ሊያከናውኑ ቀርቶ እርሱን የመሰለ ግድብም አይተው ማወቃቸውን እንደሚጠራጠሩ ገልጸው ነበር። ለምዝበራው  ትልቅ ቀዳዳ ፈጥሯል ብዬ የማስበው ለትልቅ ብክነት ተጠያቂ ነው ተብሎ እየተነሳ ያለው ተቋም ቦርድና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በሚመለከታቸው አካላት የኦዲት፣ የቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም ተጠያቂዎችን በወቅቱ ለህግ የማቅረብ ጠንካራ ስራ አለመሰራቱን ነው። በዚህም የተነሳ ባለፉት አመታት ሀገሪቱ ምን ያህል እንደተመዘበረች እና የዘራፊዎች መጫወቻ እንደነበረች መታዘብ ይቻላል።  የዚሀ አንደምታም ሀገር የሚገነባው በእውቀትና በጥበብ እንጂ በድፍረትና በጨበጣ ያለመሆኑን ነው። ሰው እንደ አቅሙና ችሎታው መሳተፍ እንጂ ለፖለቲካ ያለውን ቅርበት በመጠቀም እውቀትም ሙያውም ሳይኖር የሀገርን ሀብት ለዘረፋና ለብክነት መዳረግ በሀገር ላይ እንደመቀለድ ነው። ባለፉት አመታት ጥቂቶች ያለ በቂ እውቀትና ችሎታ እንዳሻቸው የሚፈልጉትን በሚያደርጉበት ሀገር፤ በአንጻሩ በተለያየ ሙያ ከፍተኛ ትምህርት፣ እውቀትና ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያውያን እንደ እንጀራ ልጅ ተቆጥረው በሀገር ጉዳይ ገሸሽ መደረጋቸው አሁን ለተፈጠረው ሁኔታ አንድ ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም። ከዚህ መማር ያለብን በማናቸውም የሀገር ልማትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዜጎች እኩል መብትና እድል ሊሰጠቸው እንደሚገባና ስራዎች ያለምንም የፖለቲካ መመዘኛ ለአዋቂዎችና ለባለሙያዎች  ብቻ መተው እንዳለበት ነው። በአሁኑ ወቅት በሙስናና በምዝበራ ተጠርጣሪዎች ላይ እየተወሰደ ላለው እርምጃ የመንግስትና የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነትና ተሳትፎ  ወሳኝ ነው። እርምጃው ከመጀመሩ ከጥቂት ወራት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር አስፈጻሚው አካል ያለ አግባብ ጡንቻው ፈርጥሞ ተጽአኖ እያሳደረ  በመሆኑ ፓርላማው በጥብቅ እንዲቆጣጠረን እንፈልጋለን ብለው በይፋ  ተናግረው ነበር።  ይህ ፓርላማው አስፈጻሚውን አካል በልጓም እንዲይዝ ያለውን ፈቃደኝነት ያመለክታል። መንግስት በህግ የበላይነትና ፍትህ መስፈን  ያለው ይሁንታና በጎ ፈቃደኝነት ሌላው ማሳያ በዜጎች ሰብአዊ መብትና አካላዊ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ስቃይን ያስከተሉ እንደ ጸረ-ሽብር አዋጅ የመሳሰሉ ህጎችን ለማሻሻል የተጀመረው የሪፎርም ስራ ነው። የፍትህ ስርአቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግራሉ ወይም መሰረታዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ የሚታመንባቸው፣ ሀቀኛ፣ ገለልተኛ እንዲሁም ችግሮችን ተጋፍጠው ከፊት የሚቆሙ ሰዎች እንዲሾሙ  ማድረግ የለውጥ ሀይሉና የመንግስት የቁርጠኝነት ደረጃ መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል። ለምሳሌ፡- ወይዘሮ መአዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ህብረተሰቡ፣ ሲቪል ማህበራት፣ ሚዲያው…ወዘተ አሁን በተጀመረው የሙስና ትግል ላይ እምነት እንዲኖራቸውና ተሳትፏቸውንም የበለጠ እንዲያጠናክሩ የሚገፋፋ ጥሩ ጅማሮ  መኖሩ  እየታ ነው። ቀደም ሲል የሰብአዊ መብት ጥሰቱና የአፈናው ዳፋ በይበልጥ ያርፍ የነበረው የመንግስት ብልሹ አሰራሮችን በመነቀስ በድፍረት ይተቹና ይሞግቱ የነበሩ ግለሰቦች፣ ሲቪል ማህበራትና ጋዜጠኞች ላይ ነበር። ይህ ይደረግ የነበረው ከመንግስት ጋር የፖለቲካ ትስስር ያለውና በሙስና የተደራጀው ሀይል እራሱን ለመደበቅ ሲል የሚያደርገው እንደሆነ መገመት ይቻላል። ማህበራትን ለማቀጨጭ፣ ሚዲያዎችንና ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም የወጡ የተለያዩ ህጎች ሉአላዊነትንና የሀገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚል ሽፋን ይሰጣቸው እንጂ በአመዛኙ ግባቸው የሙስናና ሌብነት መረጃ ይፋ እንዳይወጣ ለመከላከል ነበር። ህገወጥ ተግባሮችን የሚተቹ አካላት ደግሞ ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ፣ እንዲሸማቀቁና ከፍተኛ ግፍ እንዲደርስባቸው ስደረግ ነው የቆየው። ይህ የሚያሳየው ሲፈጸሙ የነበሩት የሙስና ድርጊቶች ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች የራሱ ድርሻ እንዳለው ነው። አሁን እየተፈጠረ ያለው ምቹ የዲሞክራሲ ምህዳር፣  በሙስና ላይ እየታየ ያለው የማያወላዳ ዘመቻ፤ ሲቪል ማህበራትን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መገናኛ ብዙሀንን እና  ህዝቡን የሚያነቃቃ ነው። ይህ ጅምር ሲቪል ማህበራትና የብዙሀን መገናኛዎች ብልሹ አሰራርና  የሀብት ምዝበራን ያለምንም ፍርሀትና መሸማቀቅ እንዲተቹ፤ በምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲያጋልጡ እንዲሁም ሙስና የሚያስከትለውን ጉዳት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ ጥርጊያ መንገድ ከፍቶላቸዋል።  ሀገራቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ዜጎች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮች…ወዘተ ያለፈው ብልሹና አድሎአዊ  አሰራር ካሳደረባቸው መሸማቀቅ ወጥተው የሚበረታቱበት ምቹ ሁኔታን ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ህዝቡ በለውጡ ላይ ያላቸውን እምነት ያጠናክራል፡፡ እርምጃዎቹ ለሰላማችን፣ ለልማታችን እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ያላቸው ትርጉምም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የሙስናና ብልሹ አሰራር ስሩ ሲነቃቀል የሀገር ሀብት ጥቂቶች እንዳሻቸው ማድረግ ያበቃና ህዝቡ በሀብቱና ንብረቱ ተጠቃሚ የመሆን እድሉ እየሰፋ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄም ቀስ በቀስ ምላሽ ያገኛል። የጤና፣ የትምህርት፣ የመጠለያ..ወዘተ መሰረታዊ አገልግሎቶች በመስፋፋት ህዝቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆነ የስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች በሂደት መፍትሄ እያገኙ ይሄዳሉ ማለት ነው። ህዝቡ  የሚያካሂደው ልማት የእኔ ነው ብሎ ስለሚያምን  በልማቱ በመሳተፍና  የሚጠበቅበትን ግብር ለመክፈል አያቅማማም። ዲሞክራሲም ቢሆን ከዜጎች ተሳትፎ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የኢትዮጵያም ሆነ  የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከፍተኛ ሙስናና ምዝበራ በተስፋፋባቸው ሀገሮች  በልማትና ሌሎች እንቅስቃሴ ውስጥ የብዙሀኑ ተሳትፎ አይበረታታም። እውነተኛ ዲሞክራሲ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሀዊነትና የህዝብ ተሳትፎን በመሳሰሉ መልካም እሴቶች የሚገነባና የሚተገበር የፖለቲካ ስርአት በመሆኑ በሙስናና በሌብነት የተዘፈቁ ግለሰቦችና ቡድኖች የእነዚህን እሴቶች መተግበር አይፈልጉም። ይልቁንም የተጠያቂነትና የግልጸኝነት አሰራሮችና ስርአቶች እንዳይሰፍኑ በማድረግ ዲሞክራሲው ወደኋላ እንዲጎተት የተቻላቸውን  ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህም ሌላ የፖለቲካ ትስስራቸውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የመንግስትን የሀብት ብክነትና ለስልጣን ብልግናን የሚያጋልጡ ሲቪል ማህበራትና ጋዜጠኞች እንዲታፈኑና  ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ የተቻላቸውን ያደርጋሉ። የዲሞክራሲ ሂደቱና እንዲቀጭና ምህዳሩ እንዲጠብ በማድረግ የስርዓቱ ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ፤ የሀገር ሰላምና መረጋጋትን ያደፈርሳሉ። ሀገሪቱ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት ሀገራችን  የገባችበት ውጥረት መንስኤው ከዚህ እና  ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ የተከሰተ ነው። ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መንግስት እርምጃ በመጀመሩ  በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ የሚገኙት ግጭቶች  ጥቅማቸው የተነካባቸው ሀይሎች የተለያዩ ድጋፍ በማድረግ  እራሳቸውን  ከተጠያቂነት ለማዳን የሚያደርጉት ትግል እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል። በዘረፋና በከፍተኛ ምዝበራ የተሳተፉ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ሲደረግ ሰላምና መረጋጋቱም አስተማማኝ መሠረት ይኖረዋል።  በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በሌብነት የሚጠረጠሩ አመራሮች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እስከ ታችኛው እርከን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ። መንግስት ቀንደኛ የሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎችን እያደነ ባለበት ወቅት እርምጃው የተወሰነ ብሄር ወይም የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠረና  የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳለ በማስመሰል ሀሰተኛ አሉባልታ የሚያሰራጩ አንዳንድ ግለሰቦችና የፖለቲካ አመራሮችን እያየን ነው። መንግስትም እርምጃው ግለሰቦች ባጠፉት ጥፋት እንጂ  የብሔር መልክ አለው ብለው ለሚያነሱ ሃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በቁጥጥር ስር የዋለ አንድ ተጠርጣሪ  በአግባቡ መብቱ ተጠብቆለት ለፍርድ መቅረቡና አለመቅረቡ ላይ ጥያቄ ማንሳት ተገቢና ህገ መንግስታዊ መብት ሆኖ ሳለ «እከሌ ያገሬ ሰው ስለሆነ» እንዴት በከፍተኛ ምዝበራ ታሰረ ብሎ ህዝብን መቀስቀስና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት እጅግ አሳፋሪና ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ወንጀለኛ በብሔሩ፣ በቀለሙና በሃይማኖቱ ወይም በማንነቱ  ሳይሆን በሰራው ወንጀል ልክ መጠየቅና መቀጣት አለበት። እከሌ ምን ወንጀል ሰራ እንጂ እከሌ የማን ብሄር ነው የሚል ጥያቄም መቅረብ የለበትም። ለተጀመረው ለውጥም የሚበጅ ባለመሆኑ ሰከን ብለን የህግ ሂደቱንና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ብናግዝ የተሻለ ነው። መንግስት በተደጋገሚ እንደገለጸው በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ወራቶችን ወስዶ ምርመራና የተደራጀ መረጃ አሰባስቧል፤ ይሄን ተግባሩን ካጠናቀቀ በኋላም ነው  ወደ እርምጃ የገባው። ከዚህ የምንረዳው እርምጃው በዘፈቀደ የተወሰኑ ሰዎችን ለማጥቃት አልሞ ሳይሆን ከሞላ ጎደል ህግና ስርአቱን ተከትሎ እየተፈጸመ ነው። እንደ እኔ አመለካከት ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው እርምጃው በትክክለኛው መንገድ የሚነግዱ፣ ጥረው ግረው ያገኙትን ሀብት ለጠቃሚ አላማ የሚያውሉትን ስጋት ላይ እንዳይጥልና ማህበረሰቡ ሃብት ያለውን ሁሉ እንደሌባ እንዳይቆጥር ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እርምጃው የታለመለትን ዓላማ ከሳተና ባለ ሃብቶች ላይ ስጋት ከፈጠረ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጠራል፣ ኢንቨስትመንቶችም የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ስለጉዳዩ  አስቀድሞ ዘጋቢ ፊልም መስራትና በቴሌቪዥን አየር ላይ ማዋል ሌላው ሊገታና ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ ነው። ሀሳቤን ለመቋጨት ያለፈው ትውልድ ሀገርን ከውጪ ወራሪዎች ጠብቆ፤ ሀገርን ከሚጎዱ ተግባራት ጭምር ተቆጥበው ኢትዮጵያን ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡ መሆኑን በመዘንጋት የሀገርን ሀብት ሀላፊነት በጎደለው  መልኩ መመዝበር የመጪውን ትውልድ ተስፋና እድል ማጨናገፍ መሆኑን መረዳት አለብን። የአሁኑ ትውልውም ለመጪው ትውልድ ማውረስ ያለበት እዳ እና የተወሳሰበ ችግር ሳይሆን በቂ ሀብትና የተሻለች  ሀገርን ነው የሚል እምነት አለኝ ። ቸር ያሰማን!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም