ወደ ኤርትራ በመጓዝ ላይ ያሉት ‘‘የሰላም ቱር‘‘ ኢትዮጵያዊያን ብስክሌተኞች ዛሬ መቀሌ ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

472

መቀሌ ህዳር 20/2011 ከአዲስ አበባ ወደ ኤርትራ በመጓዝ ላይ ያሉት ‘‘የሰላም ቱር‘‘ ኢትዮጵያዊያን ብስክሌተኞች ዛሬ መቀሌ ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

ስፖርተኞች  ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ተኩል መቀሌ ከተማ ሲገቡ የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ገብረማርያም ዘሚኪኤል ጉንጉን አበባ አጥልቀውላቿዋል።

ዳይሬክተሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፣ ‘‘የሰላም ቱር‘‘ የብስክሌት ተጓዦቹ በኢትዮጰያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር አምባሳደር ሆነው መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል።

ከተጓዦቹ መካከል አዲስ አበባ መስተዳድርን ወክሎ የተሳተፈው ብስክሌተኛ ወጣት ቢንያም ብርሀኑ  ”የሰላም ግንኙነት ለመሪዎች ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ኢትዮጰያን ወክለን ለሰላምና አንድነት ጉዞውን እያካሄድን ነው” ብሏል።

አማራ ክልልን ወክሎ የሰላም ቱሩ የብስክሌት ውድድሩ ተካፋይ የሆነው ወጣት ብስክሌተኛ ፈጠነ ተመስገን በበኩሉ  ከአዲስ አበባ ተነስተው ያለምንም ችግር መቀሌ ከተማ መድረሳቸውን ገልጿል፡፡

መቀሌ ሲገቡም የከተማው ህዝብ ባደረገላቸው ደማቅ አቀባበል መደሰቱን ተናግሯል።

የሰላም ቱር ብስክሌተኞች መነሻቸውን መቀሌ ከተማ በማድረግ አስመራና ባጽእ 405 ኪሎ ሜትር ርቀት ይሸፍናል።

ውድድሩን እስከ ፍጻሜው ድረስ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፌዴራል ፖሊስና የፀጥታ አባላት ተገቢውን ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውምን ለማወቅ ተችሏል።

በሚካሄደው የሰላም ቱር የብስክሌት ውድድር ላይ የድሬዳዋና አዲስ አበባ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተወጣጡ ከ30 በላይ ኮርሰኞችን በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡