መከላከያ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከናይጄሪያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ጋር ይገጥማል

57
አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊው መከላከያ በ2018/19 አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከናይጄሪያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ጋር ዛሬ ይካሄዳል። የዘንድሮው ዓመት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የውድድር ዘመን ዛሬ በሚደረጉ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይጀመራል። በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው መከላከያ 33 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው የናይጄሪያው ናምዲ አዚኪዌ ስታዲየም ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ከኢኒጉ ሬንጀርስ ጋር የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። አሰልጣኝ ስዩም 18 ተጫዋቾችን ይዞ ወደ ናይጄሪያ ማምራቱ የሚታወስ ነው። መከላከያ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍና የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን በባለፈው የውድድር ዓመት ያስመዘገበው ስኬት ቡድኑን በጥሩ መነቃቃት ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባደረገው አንድ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ 2 ለ 1 በማሸነፍ ባገኘው ሶስት ነጥብ በፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ፍጹም ገብረማርያም፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ምንይሉ ወንድሙ፣ ሳሙኤል ታዬና ፍሬው ሰለሞን በቡድኑ ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ ተጫዋቾች ሲሆኑ በዛሬው ጨዋታም ለመከላከያ ውጤት ይዞ መውጣት ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። መከላከያ በዛሬው ጨዋታ ውጤት ይዞ ለመውጣት በአጥቂ መስመር ላይ ያለውን የአጨራረስ ድክመት መቅረፍ ይኖርበታል። መከላከያ የዘንድሮው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎው በአራት ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በራሪዎቹ ሚዳቆዎች  የሚል መጠሪያ ያለው ኢኑጉ ሬንጀርስ የናይጄሪያ ፕሪሚየር ሊግን ሰባት ጊዜ፤ የናይጄሪያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ስድስት ጊዜ ያነሳ ሲሆን የናይጄሪያን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አንድ ጊዜ ያሸነፈ ክለብ ነው። በተጨማሪም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1977 የአፍሪካ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል። በ55 ዓመቱ ናይጄሪያዊው ግቤንጋ ኦጎንቦቴ የሚመራው ኢኒጉ ሬንጀርስ በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ናይጄሪያውያኖቹ ሰለሞን ኦክፓኮ፣ቻርለስ ኔጌዱ፣ፎርቹን ኦሞኒዋሪ፣ጎድዊን ዛኪ እና ቤኒናዊው ኢሳክ ሉት በኢኒጉ ሬንጀርስ በኩል ቁልፍ የሚባሉ ተጫዋቾች ናቸው። ከጨዋታው በፊት ኢኒጉ ሬንጀርስ ክለብ ተጋጣሚው መከላከያ ወደ ናይጄሪያ ስለሚያደርገው ጉዞ ከክለቡና ከናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንም አይነት ይፋዊ ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ አለማድረጉ እንዳላስደሰታቸው አስታውቀዋል። ያም ቢሆን መከላከያ በናይጄሪያ በሚኖረው ቆይታ የሚያስፈልገውን ትብብር እንደሚያደርግ ክለቡ ገልጿል። ጦሩ በሚል ስያሜ የሚታወቀው መከላከያ በራሪዎቹ ሚዳቆዎቹ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኒጀራዊው አሊ ሙሳ መሐመድ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። መከላከያ የመልስ ጨዋታውንም ህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርግ ሲሆን መከላከያ የደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ከአልጄሪያው ዩኤስኤምቤል አቤስ ወይም ከላይቤሪያው ኤልአይኤስሲአር አሸናፊ ጋር ይጫወታል። በሌላ በኩል ትናንት በ2018/19 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን በጅቡቲ ያደረገው ጅማ አባ ጅፋር ተጋጣሚውን ጅቡቲ ቴሌኮምን በአስቻለው ግርማ አንድ ጎልና በማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤ ሁለት ጎሎች 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጭ ባስመዘገበው ውጤት የማለፍ እድሉን በከፍተኛ ሁኔታ ያሰፋ ሲሆን የመልስ ጨዋታውን ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል። ጅማ አባ ጅፋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ ከባለፈው ዓመት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ከነበረው የግብጹ አል አህሊ ጋር በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ይጫወታል። የዘንድሮው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ለ55ኛ፤ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም