የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የፕሪሚሪሊግ ውድድሩን በአዲስ አቀራረብ ሊያካሂድ ነው

72
አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ 6ኛውን አገር አቀፍ ክለቦች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በአዲስ አቀራረብ ሊያካሂድ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ቅርጫት ፌዴሬሽን ዛሬ ከክለቦች ጋር ባካሄደው ውይይት እንዳስታወቀው ባለፉት አምስት ዓመታት ውድድሩ ይካሄድ የነበረው ሁሉንም ክለቦች በአንድ ምድብ በማካተት በዙር እንደነበር ገልጿል። በዚህ ዓመት ግን በመጀመሪያው ምዕራፍ ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው በዙር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ነው የተባለው። በሁለቱ ምድቦች አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ ክለቦች በአንድ ምድብ፤  ሶስተኛና አራተኛ የሚወጡ ክለቦች ደግሞ በሌላ ተደልድለው እንዲጫወቱ ይደረጋል። ይህን አዲስ አሰራር መከተል ያስፈለገው ክለቦች ብዙ ውድድሮችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማካሄድ እንዲችሉ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል። በኢትዮጵያ ቅርጯት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በወንዶች ከስምንት እስከ  ዘጠኝ በሴቶች ደግሞ ከስድስት እስከ ሰባት ክለቦች ይካፈላሉ። በድልድሉ ውስጥ በዚህ ዓመት በአዲስ የሚካፈሉ ክለቦች መኖራቸውም ተገልጿል። በድልድሉ ገብተው ሆኖም  መሳተፍ ወይም አለመሳተፋቸውን ለፌዴሬሽኑያላሳወቁ ክለቦች መኖራቸውም ተመልክቷል። በዚህ መሰረትም በወንዶች ውድድር በምድብ ''ሀ''  ሀዋሳ ከተማ ፣ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ፣አዳማ ከተማ፣ ድሬድዋ ከተማና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ተደልድለዋል። በምድብ ''ለ'' ደግሞ ወልቂጤ ከተማ፣ ጎንደር ከተማ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና የካ ክፍለ ከተማ ተደልድለዋል። በሴቶች ደግሞ በምድብ ''ሀ ''ጎንደር ከተማ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ሀዋሳ ከተማ የተደለደሉ ሲሆን በምደብ ''ለ '' ደግሞ ወልቂጤ ከተማ፣ ባህርዳር እና ቢጂይ ኢትዮጵያ ተደልድለዋል። ውድድሩ በመጪው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ሳምንት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም