በኦዲት ግኝቶች መሰረት የማስተካከያ እርምጃ የማይወሰዱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሊከሰሱ ነው

4046

አዲስ አበባ ግንቦት 16 /2010 በኦዲት ግኝቶች መሰረት የማስተካከያ እርምጃ የማያደርጉ የመንግስት ተቋማትን ለህግ እንደሚያቀርብ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

ተቋሙ የ2009 በጀት ዓመት ሂሳብና ክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በ2009 በጀት ዓመት የ173 ባለበጀት የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና 48 ቅርንጫፎቻቸው ኦዲት ተደርጎ ሪፖርት ተልኮላቸዋል።

ከእነዚህ መካከልም 25ቱ ነቃፌታ የሌለው አስተያየት የተሰጣቸው ሲሆን 87ቱ ከጥቂት ጉድለት በስተቀር አጥጋቢ ሆነው ተገኝተዋል። ሌሎች 53 ተቋማት ግን የጎላ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።

ዋና ኦዲተሩ እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ በአምስት መስሪያ ቤቶች ከ927 ሺህ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ታይቷል።

ይህ የገንዘብ ጉድለት ከታየባቸው መስሪያ ቤቶች መካከል ጋምቤላና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ፣ ደንና አየር ለውጥ ሚኒስቴር እንዲሁም ምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲውቲካል ኢንስቲትዩት እንደሆኑ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ በየመስሪያ ቤቶቹ በህግ መሰረት ያልተወራረደ 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መገኘቱን የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት አመልክቷል።

የአዲስ አበባ፣ ዋቸሞና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ብሄራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ እና እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴሮች ግኝቱ ጎልቶ የታየባቸው ናቸው።

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና 10 ቅርንጫፎቹ እንዲሁም በሌሎች 49 መስሪያ ቤቶች ከገቢ ግብር፣ ከቀረጥና ታክስ መሰብሰብ የነበረበት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ሳይሰበሰብ መቅረቱን ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል።

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ዘጠኝ ቅርጫፎቹ በወቅቱ ያልተሰበሰበና መሰብሰብ የሚገባው 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገቢ መኖሩም ተመልክቷል።

ከዚህ ሌላ ባለስልጣኑ በባህርዳር ቅርጫፍ መስሪያ ቤት በኩል የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅሬታ ቶሎ መፈታት ባለመቻሉ መሰብሰብ የነበረበት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር  ውዝፍ ሆኖበታል።

የወጪ ሂሳብን በተመለከተ በአዲስ አበባ፣ በዲላ፣ በአክሱምና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣንና በሌሎች 68 መስሪያ ቤቶች ከ506 ሚሊዮን ብር በላይ የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ በውጪ ተመዝግቦ መገኘቱን ሪፖርቱ አትቷል።

በ98 ተቋማት ደግሞ 199 ሚሊዮን የሚጠጋ ብርና ከ49 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ያልተገባ ክፍያ ተፈፅሞ ተገኝቷል።

በተጨማሪም በ97 መስሪያ ቤቶችና ስድስት ቅርንጫፎቻቸው የመንግስትን የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ከ487 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስወጣ ግዥ ተከናውኗል።

የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ደግሞ በ41 መስሪያ ቤቶች በልዩ ልዩ ሂሳቦች 898 ሚሊዮን ብር ከተደለደለ በጀት በላይ ወጪ አድርገው መገኘታቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም እንዲሁም አዲስ አበባ፣ ወልዲያ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ከበጀት በላይ ወጪ በማድረግ የኦዲት ግኝቱ ካመላከታቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የመንግስት ተቋማት ከፋይናንስ በተጨማሪ ንብረት በማስተዳደር ረገድ ተመሳሳይ ክፍተቶች እንደሚታይባቸው ነው ዋና ኦዲተሩ ያብራሩት።

‘ችግሩ በየዓመቱ ከመስተካከል ይልቅ እየተባባሰ መጥቷል’ በሚል ከምክር ቤቱ አባላት የተጠየቁት ዋና ኦዲተር ገመቹ መስሪያ ቤቶች ”ጠቅሞናል፣ ተምረንበታል” ከማለት ባለፈ የተሰጣቸውን አስተያየት ተቀብሎ ማስተካከል ላይ ሰፊ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በኦዲት ግኝቶች መሰረት የማስተካከያ እርምጃ የማይወስዱ የመንግስት ተቋማትን ከፌዴራል ዐቃቤ ህግ ጋር በመተባበር ለህግ እንደሚያቀርብ ዋና ኦዲተሩ አስታውቋል።